ቀጥታ፡

መንግስት የጀመረውን ሁለንተናዊ ዕድገት ዳር እንዲደርስ  ሰላምን መጠበቅ የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት ነው

ደሴ፤ ግንቦት 18/2016(ኢዜአ)፦መንግስት የጀመረውን ሁለንተናዊ ዕድገት ዳር እንዲደርስ  ሰላምን መጠበቅ የሁሉም ዜጋ  ሃላፊነት  መሆኑን  የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሐጅ ኢብራሂም ቱፋ ገለጹ። 

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለአገራችን ችግሮች ዘላቂ መፍትሄን የሚያስገኝ በመሆኑ መደገፍ እንደሚገባም የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ገልጸዋል።

 "አንድነታችን ለሰላማችን" በሚል መሪ ሃሳብ አገር አቀፍ የሰላም፣ የአብሮነትና የወንድማማችነት ኮንፈረንስ በኮምቦልቻ ከተማ ተካሄዷል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሐጅ ኢብራሂም ቱፋ የለውጡ መንግስት የጀመረው ሁለተናዊ ዕድገት ዳር እንዲደርስ ከመንግስት ጎን በመቆም  ሰላምን መጠበቅም የሁላችንም ሃላፊነት መሆን አለበት ብለዋል። 

ህዝበ ሙስሊሙ ከሁሉም በፊት አንድነታችንን ጠብቀን ሰላማችንን ማጠናከር ይኖርብናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ ከሌሎች እምነቶች ጋር ተከባብሮና ተቀናጅቶ ሰላምን መጠበቅና አጥፊዎችን መገሰጽ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የእምነት ተቋማትም መከፋፈልን፣ ጥላቻንና ግጭትን በማውገዝ፣ ለሰላም፣ ለአንድነትና ለልማት ምዕመናቸውን በማስተማር ሚናቸውን በተግባር እንዲወጡም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለአገራችን ችግሮች ዘላቂ መፍትሄን የሚያስገኝ መሆኑን ጠቁመው፤ የእርሱን ተግባር መደገፍ፣ ግብዓት መስጠት፣ መሳተፍና በማንኛውም ጉዳይ ማገዝ እንደሚገባም አመልክተዋል።


 

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዱ ሁሴን በበኩላቸው በኮንፈረንሱ ላይ ባስተላለፉት መልእክት እንደገለጹት፤ የአማራ ክልል ዘላቂ ሰላም ለማስጠበቅ ሁሉም እምነቶች አንድነታቸውን ጠብቀው ለሰላምና ለልማት መስራት ይጠበቅባቸዋል። 

የሁሉም እምነቶች አስተምህሮ ወንድማማችነት፣ መረዳዳት፣ መተጋገዝና ፍቅር እንዲጎለብት እንደሚያስተምር ያስታወሱት አቶ አብዱ፤ ይህም የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት አቅም እንደሚሆን ተናግረዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም