የስትራይድ ኢትዮጵያ ኤክስፖ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ በምርምርና ኢኖቬሽን የተከናወኑ ተግባራትን በስፋት ያስተዋወቀ ነው- በለጠ ሞላ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 18/2016(ኢዜአ)፦የስትራይድ ኢትዮጵያ 2024 ኤክስፖ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ በምርምርና ኢኖቬሽን የተከናወኑ ተግባራትን በስፋት ያስተዋወቀ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ።

ከግንቦት 11 እስከ 18 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በሳይንስ ሙዚየም ሲካሄድ የቆየው ስትራይድ ኢትዮጵያ  2024 ኤክስፖ የማጠናቀቂያ ፕሮግራም ተካሂዷል።

የኤክስፖው መክፈቻ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአይሲቲ ፓርክ የተካሄደ ሲሆን በሳይንስ ሙዚየም ደግሞ ለእይታ ክፍት ሆኖ ቆይቷል።

ኤክስፖው  "ሳይንስ በር ይከፍታል፤ ቴክኖሎጂ ያስተሳስራል፤ ፈጠራ ወደፊት ያራምዳል" በሚል መሪ ሃሳብ"  ተካሂዶ በዛሬው እለት ተጠናቋል።

በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ንግግር ያደረጉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፤ ኤክስፖው ኢትዮጵያ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ በምርምርና ኢኖቬሽን የተከናወኑ ተግባራትን በስፋት ያስተዋወቀ ነው ብለዋል።


 

በኤክስፖው በርካታ ልምዶች የተገኙበት በቴክኖሎጂ የታገዙ አዳዲስ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ወጣቶች የታዩበትና የተበረታቱበት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የግል ድርጅቶች ተሳትፎ የታየበት ኤክስፖ እንደነበር ጠቅሰው ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይሰራል ብለዋል።

የስራና ክሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል፣ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብረሃኑ ነጋ እና ሌሎችም የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመዝጊያ ስነ ስርአቱ ላይ ተገኝተዋል።

በማጠቃለያ መርሃ-ግብሩ ላይ ለዘርፍ አስተዋጽኦ ላደረጉና ተጨባጭ ውጤት ላስገኙ ሽልማትና ዕውቅና ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም