ሀገራዊ ልማትና እድገትን ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት የወጣቶች የፈጠራ ሚና ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 18/2016 (ኢዜአ):- ሀገራዊ ልማትና እድገትን ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት የወጣቶች የፈጠራ ሚና ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ "በፈጠራ ስራ የዳበረ ትውልድ ለሁለንተናዊ እድገትና ብልፅግና" በሚል መሪ ሀሳብ ሲካሄድ የቆየው 9ኛው ከተማ አቀፍ የሳይንስና የፈጠራ አውደ ርዕይ ማጠቃለያ ፕሮግራም ተካሂዷል።

በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ፤ የወጣቶች ሳይንስና ፈጠራ ለሀገር እድገትና ብልጽግና ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም የተማሪዎች የፈጠራ ሥራዎች ሀገራዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ መሰረቶች መሆናቸውን ጠቅሰው በፈጠራና በቴክኖሎጂ በመታገዝ ሀገራዊ ልማትና እድገትን ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት የወጣቶች ሚና ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

የትምህርት ቤቶችን ደረጃና ጥራት ማሻሻል፤ የትምህርት ቤት የምገባ ሥርዓት፣ የመማር ማስተማሪያ ግብዓትና የንድፈ ሀሳብ አቅም የፈጠራ አቅምንም የሚያሳድጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡


 

ከተማ አስተዳደሩ ንድፈ ሀሳቦችን ከተግባር ትምህርት ጋር በማቀናጀት የተማሪዎችን የመፍጠር አቅም ለማሳደግ የጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የትምህርት ቤቶች የፈጠራና የምርምር ውጤቶች የሀገር እድገት መሆናቸውን ገልጸው፤ የምርምር ሥራዎች ወደ ተግባር እንዲለወጡ የጋራ ርብርብ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ፤ አውደ ርዕይው የተማሪዎችን የፈጠራ ክህሎት ለማሳደግ፣ ልምድ ለመጋራትና ስራዎቻቸውን ለማስተዋወቅ ትልቅ እድል የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የተማሪዎችን የፈጠራ አቅም የሚያጎለብቱ መርሃ ግብሮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡

በዛሬው መርሃ ግብር የላቀ የሳይንስና የፈጠራ ውጤቶችን በማቅረብ አሸናፊ ለሆኑ ትምህርት ቤቶች የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም