የበርበራን ኢኮኖሚ ኮሪደር መጠቀም ለቀጠናው ህዝቦች ትስስር የሚኖረው ጠቀሜታ የጎላነው - አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ - ኢዜአ አማርኛ
የበርበራን ኢኮኖሚ ኮሪደር መጠቀም ለቀጠናው ህዝቦች ትስስር የሚኖረው ጠቀሜታ የጎላነው - አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ
ጅግጅጋ፤ ግንቦት 18/2016 (ኢዜአ)፦ የበርበራን ኢኮኖሚክ ኮሪደር መጠቀም ለቀጠናው ህዝቦች ትስስር የሚኖረው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ ተናገሩ።
ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ከጅግጅጋ ከተማ አስተዳደርና ከኢትዮጵያ ከተሞች መድረክ ጋር በመተባበር የበርበራ ኢኮኖሚክ ኮሪደር እና የሰዎች እንቅስቃሴ በሚል ርዕሰ ያዘጋጁት ፓናል ውይይት በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በፓናል ውይይቱ በሶማሌላንድ የሀርጌይሳ ከተማ ከንቲባ አቶ አብዱካሪም አህመድ ሞጌ፣ የበርበራ ከተማ ከንቲባ አቶ አብድ ሸኩር መሐመድ፣ የቦረማ ከተማ ከንቲባ አቶ መሐመድ አህመድ ዋርሳሜና የጋቢላይ ከተማ ከንቲባ አቶ መሐመድ አሚን ኦማር ታድመዋል።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ እና የጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌን ጨምሮ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴርና የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ አመራር አባላትም ተሳታፊ ሆነዋል።
የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ በፓናሉ ላይ እንደገለጹት፤ የበርበራን ኢኮኖሚክ ኮሪደር መጠቀም በቀጠናው ለህዝቦች ትስስር መጎልበት ፋይደው የጎላ ነው።
በተጨማሪም ለህዝቦች የሚኖረው የወደብ እና የባህር ትራንስፖርት አገልግሎት ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።
የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ሰብሳቢና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌ በበኩላቸው በበርበራ ኮሪደር ላይ የሚከናወኑ የልማት ተግባራት የአፍሪካን የንግድ፣ የአገልግሎትና፣ የካፒታል ዝውውርን ለማሳለጥ ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።
በቀጠናው የሚከናወን የንግድ እና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን በማሳደግ የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 እቅዶችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚኖረው ሚናም የጎላ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በመድረኩ የሶማሌ ላንድና የኢትዮጵያ ምሁራን የበርበራ ኢኮኖሚክ ኮሪደር ለቀጠናው ያለው ፋይዳ፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦት፣ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኘው መንገድ እና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎችን የሚዳስሱ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ታውቋል።