በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ26ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ26ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 18/2016 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ26ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ኢትዮጵያ ቡና ከሀምበሪቾ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
በአሰልጣኝ ነጻነት ክብሬ የሚመራው ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ ካደረጋቸው ያለፉት 5 ተከታታይ ጨዋታዎች 2 ጊዜ ሲያሸንፍ 1 ጊዜ ተሸንፏል። 2 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
ቡናማዎቹ በነዚህ 5 ጨዋታዎች 7 ጎሎችን ሲያስቆጥሩ 6 ግቦችን አስተናግደዋል።
ኢትዮጵያ ቡና በ41 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ሀምበሪቾ ካለፉት 5 የሊግ ጨዋታዎች በ4ቱ ሲሸነፍ 1 ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። በ5ቱ ጨዋታዎች ያስቆጠረው 2 ግቦችን ሲሆን 9 ጎሎችን አስተናግዷል።
በብሩክ ሲሳይ የሚሰለጥነው ሀምበሪቾ በ8 ነጥብ የመጨረሻውን 16ኛ ደረጃ ይዟል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ነው።
በ26ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ ግብር ሀድያ ሆሳዕና ከሃዋሳ ከተማ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።
ሀድያ ሆሳዕና ካለፉት 5 የሊግ ጨዋታዎች ያሸነፈው 1 ጊዜ ብቻ ነው። 2 ጊዜ ሲሸነፍ በተመሳሳይ 2 ጊዜ አቻ ወጥቷል። ሀድያ በ5ቱ ጨዋታዎች 6 ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ 6 ጎሎችን አስተናግዷል።
በአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ የሚመራው ሀድያ ሆሳዕና በ35 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ተጋጣሚው ሃዋሳ ከተማ በበኩሉ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት 5 ተከታታይ ጨዌታዎች 2 ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ 2 ጊዜ ተሸንፏል። 1 ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።
ክለቡ በነዚህ 5 ጨዋታዎች 7 ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ 7 ግቦችን አስተናግዷል።
በዘርዓይ ሙሉ የሚሰለጥነው ሃዋሳ ከተማ በ33 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ መለያየታቸው ይታወሳል።
በተያያዘም ትናንት በተደረጉ የ26ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፋሲል ከነማን እንዲሁም ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲዳማ ቡናን በተመሳሳይ 1 ለ 0 አሸንፈዋል።
የ27ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የ26ኛው የዓለም ማጣሪያ ጨዋታ ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን ከፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማህበር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።