የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር በ60 ቀናት ዕቅድ አተገባበር ላይ ውጤታማ የልማት ተግባራት ማከናወኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር በ60 ቀናት ዕቅድ አተገባበር ላይ ውጤታማ የልማት ተግባራት ማከናወኑን ገለጸ

ባህር ዳር ፤ግንቦት 17/2016 (ኢዜአ)፡- የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር በ60 ቀናት የዕቅድ አተገባበር ላይ ሰላምን በማፅናት ውጤታማ የልማት ተግባራት ማከናወን መቻሉን የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ገለጹ።
ከተማ አስተዳደሩ የ60 ቀናት ዕቅድ አፈፃፀም የሚገመግም መድረክ በባህር ዳር ከተማ አካሄዷል።
በዚህ ወቅት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አቶ ጎሹ እንዳላማው እንዳሉት፤ የከተማው ህዝብ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በመለየት ለመፍታት ሰፊ ጥረት ተደርጓል።
በዚህም አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን እስከ ቀበሌ ድረስ የፀጥታ መዋቅሩን እንደገና በማደራጀት በተደረገ ስምሪት ውጤታማ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።
በዚህም ሰላምን በማፅናት ምቹ ሁኔታ መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል።
በመሰረተ ልማትም እየተገነባ ከሚገኝ ነባር የአስፋልት መንገድ ውስጥ 13 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትሩን በበጀት ዓመቱ መጨረሻ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
እንዲሁም 27 ኪሎ ሜትር የአዲስ መንገድ መክፈትና ጥገና ስራ በ60 ቀን ዕቅድ ማከናወን መቻሉን ጠቅሰው፤ የ7 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የመንገድ ዳር የ"ሶላር" መብራት ተከላ ስራም እየተፋጠነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ገቢን በመሰብሰብም የ60 ቀን ዕቅድን ሲጀመር 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የነበረው በአሁኑ ወቅት 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ማድረስ እንደተቻለ አመልክተዋል።
የአረንጓዴ ልማት ለማስፋፋት፣ የኑሮ ውድነትን ለማቃለልና ሌሎች የተከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራትም በውጤታማነት መፈፀም እንደተቻለ አስረድተዋል።
በ60 ቀን ዕቅድ የተጀመረው የከንቲባ ችሎት ሲንከባለሉ የቆዩ ከ84 በላይ ቅሬታዎች እልባት እንዲያገኙ በማድረግ የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ማቃለል መቻሉንም አነሰተዋል።
በአፈፃፀም ወቅት የተስተዋሉ የቅንጅት መጓደል፣ የድጋፍና ክትትል ውስንነቶች በቀጣይ የ100 ቀናት ዕቅድ ተለይተው ለማስተካከል ከወዲሁ በቂ ዝግጅት መደረጉንም አስታውቀዋል።
በባህርዳር ከተማ የአፄ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተዋበ አንለይ በበኩላቸው፤ በ60 ቀናት ዕቅድ በተከናወነ የህግ ማስከበር እንቅስቃሴ ህብረተሰቡ የሰላሙ ባለቤት እንዲሆን ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
በዚህም ህዝቡ በ18 ቀጠናዎች ተደራጅቶ የአካባቢውን ሰላም መጠበቅ እንደቻለ ጠቅሰው፤ የሰላም ማስክበርና የልማት ስራዎች በ100 ቀን እቅድም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
ህብረተሰቡ የሰላሙ ባለቤት እንዲሆን በተከናወነው ስራ ተጨባጭ ውጤት ማምጣት መቻሉን የገለጹት ደግሞ የዳግማዊ ምንሊክ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ግዛት አላምረው ናቸው።
እንዲሁም በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በመንገድ መሰረተ ልማትና በገቢ አሰባሰብ የታየውን መሻሻል በቀጣይ መቶ ቀናት ዕቅድ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ውጤታማ ስራ ለማከናወን ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
በዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረኩ የከተማ አስተዳደር፣ የክፍለ ከተማና የቀበሌ አመራር አባላት ተሳትፈዋል።