ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከግንቦት 21 ጀምሮ የምክክር ምዕራፍ ሊያካሂድ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 17/2016(ኢዜአ)፦የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የምክክር ምዕራፍ ከግንቦት 21 ጀምሮ መካሄድ እንደሚጀምር ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ገለጸ። 

በኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካና የኃሳብ መሪዎች እንዲሁም የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል እጅግ መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የኃሳብ ልዩነትና አለመግባባት በአካታች አገራዊ ምክክር ለመፍታት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሟል።   

ኮሚሽኑም ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ምክክሩን ለመጀመር የሚያስችሉትን የተለያዩ ተግባራት በገለልተኛነትና በነጻነት እያከናወነ ሲሆን በ10 ክልሎችና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች የተሳታፊ ልየታ ማጠናቀቁን ገልጿል። 

በቀጣይ ደግሞ የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የምክክር ምዕራፍ ከግንቦት 21 ጀምሮ መካሄድ እንደሚጀምር የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር አምባዬ ኦጋቶ ለኢዜአ ገልጸዋል። 

ለዚህም አስፈላጊ የሚባሉ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ ለዚህ ሂደት መሳካት ሁሉም የሚጠበቅበትን እንዲያበረክት ጠይቀዋል። 

ግንቦት 21 በሚጀመረው በዚህ የምክክር ምዕራፍ ላይ ሦስት መሰረታዊ ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል።

የክልል ባለድርሻ አካላትና ከወረዳ ተመርጠው የመጡ ሰዎች በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ይመክራሉ ያሉት ኮሚሽነሩ ኢትዮጵያ በምክክር ችግሮቿን ትፈታለች የሚል የጋራ ግንዛቤ የሚፈጥሩበት እንደሚሆንም ተናግረዋል።   

ይህ ምዕራፍ በጋራ ሆነው አጀንዳዎችን የሚመርጡበት መድረክ መሆኑን ጠቁመው ከመረጧቸው አጀንዳዎች መካከልም በቀላሉ መፍታት የሚችሉትን አጀንዳ እዛው ተመካክረው እንዲፈቱ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሥራ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በሌላ መልኩም በዚህ ምዕራፍ የመጡበትን አካባቢ ወክለው አጀንዳዎችን በመያዝ በአገር ደረጃ በሚካሄደው የምክክር ሂደት ላይ ከሌሎች ክልሎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋራ የሚመክሩ ሰዎች የሚመረጡበት መድረክ መሆኑንም ጠቁመዋል።   

በኢትዮጵያ ለዘመናት የቆዩ ችግሮችን በምክክር ለመፍታትና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ተገብቷል፤ አገራዊ ምክክሩ የተሻለች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ የላቀ ድርሻ አለው። 

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም