ቀጥታ፡

በአፋር ክልል የልማት ስራዎችን  ለማፋጠን  ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የሙያ ማህበራት እንዲያግዙ እየተደረገ ነው 

ሰመራ ፤ ግንቦት 17/2016(ኢዜአ)፦ በአፋር ክልል የልማት ስራዎችን በተሻለ መልኩ ለማፋጠን የሚደረገውን ጥረት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የሙያ ማህበራት እንዲያግዙ እየተደረገ  መሆኑን የክልሉ የፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሐሚድ ዱላ ገለጹ።

የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማህበር ጋር በመተባበር የክልሉን ኢኮኖሚ እድገት ማፋጠን ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ አካሄዷል።

በዚህ ወቅት የአፋር ክልል የፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሐሚድ ዱላ እንደተናገሩት፤ የክልሉ መንግስት የኢኮኖሚ ልማት እንቅስቃሴውን ለማፈጠን ለምሁራን ተሳትፎ ትኩረት ሰጥቷል።

ሰመራ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በኢኮኖሚ ላይ አተኩረው የሚሰሩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የሙያ ማህበራት የክልሉን ልማትና እድገት በጥናትና ምርምር እንዲያግዙ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም የጥናትና ምርምር ተቋማት በክልል ደረጃ የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን እንዲደግፉ የሚደረግ ሲሆን ይህም የክልሉን ዕድገት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገርና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።

የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አብዱራህማን ከድር፣ ዩኒቨርሲቲው በሚያካሄዳቸው የጥናትና ምርምር ስራዎች የክልሉን ልማት እየደገፈ መሆኑን ተናግረዋል።

ወደ ፊትም ዩኒቨርሲቲው ድጋፉን እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በዚህ ሂደት ደግሞ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማህበርን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንዲሳተፉ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማህበር ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር መንግስቱ ከተማ በበኩላቸው፤ ማህበሩ የተለያዩ ጥናትና ምርምሮችን ሲያካሄድ መቆየቱን አብራርተዋል።

ማህበሩ ያከናወናቸው የምርምር ስራዎች ለፖሊሲ ግብአትነት ጭምር ሲውሉ መቆየታቸውን ገልጸው፤ ስልጠናዎችንና የውይይት መድረኮችንም ሲያዘገጅ እንደነበረ ጠቁመዋል።

ማህበሩ ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን የአፋር ክልል የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ላይ ጥናትና ምርምር የሚያደርግ መሆኑን አመልክተዋል።

በውይይቱ ማጠቃለያ ወቅት ማህበሩ ከሠመራ ዮኒቨርሲቲ፣ ከክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ፣ ከክልሉ መልሶ ማቋቋም ፈንድ ጽህፈት ቤት ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል።

በውይይቱ ላይ የተለያዩ የክልሉ ቢሮ ኃላፊዎች፣ የሙያ ማህበራትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም