መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ በግብርናው ዘርፍ ለምርታማነት እድገት ሚናውን እየተወጣ ነው

ደሴ ፤ ግንቦት 17/2016(ኢዜአ)፦ መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ በግብርናው ዘርፍ አርሶ አደሮችን በምርምር በማገዝ  ለምርታማነት እድገት የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ገለጸ።

ዩኒቨርሲቲው ሁለተኛውን አገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ እያካሄደ ነው።

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጥናትና ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ስለሺ አቢ እንደገለጹት ተቋሙ ከመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን እያከናወነ ነው።



 

በግብርና፣ ቴክኖሎጂ ፣ ማዕድንና ቱሪዝም ሀብቶች ላይ 75 ጥናትና ምርምሮች እየተካሄዱ መሆኑን ጠቁመው ከእነዚህ ውስጥ በተጠናቀቁት 13 ጥናቶች ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መገኘታቸውን ተናግረዋል።

ከዚህም በተለይ  በሰብል ልማት የስንዴ፣ ሽምብራና ምስር እንዲሁም በደጋ ፍራፍሬዎች  ዝርያዎችን በማሻሻልና በማላመድ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ተናግረዋል።

በእንሰሳት ዘርፍም የበግና የዳልጋ ከብት ማድለብና እርባታ ላይ የተጀመሩ ጥናቶች አዋጪና የአርሶ አደሩን ኑሮ የሚያሻሽሉ ናቸው ብለዋል።

ከዚህም ሌላ በወሎ አካባቢ የሚገኙ በርካታ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ሀብቶችን ለይቶ በማስተዋወቅ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ እገዛ እያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው የተጀመሩ የምርምር ስራዎችም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።


 

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ የእጽዋት ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር በቃሉ አበበ በበኩላቸው በባቄላ ሰብል ላይ ባደረጉት ምርምር የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀም አሲዳማ አፈርን በማከም የአረምና የተባይ ቁጥጥር ስራ በማከናወን ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚቻል ማረጋገጥ እንደቻሉ ገልጸዋል።

የስጋ፣ የወተትና የእንቁላል ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚቻል ባቀረቡት ጥናት ያመላከቱት ደግሞ በኢትዮጵያ በዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት የለማዳ እንስሳት ተመራማሪ አቶ ተስፋለም አሰግድ ናቸው።


 

ለዚህም መንግስት በሌማት ትሩፋት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ለወጣቱ የስራ እድል መፍጠር ምርታማነትን ማሳደግና  አርሶ አደሩ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኝ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ኢንስቲትዩቱ በኢትዮጵያ  በተመረጡ 24 ማዕከላት የተለያዩ እንስሳት ዝርያዎችን በምርምር የማሻሻልና የማላመድ ተግባራት እያከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የተሻለ ምርት የሚሰጡ አዳዲስ ዝርያዎች እየተገኙ ነው ብለዋል።

በኮንፈረንሱ በአገሪቱ ከሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራን እየተሳተፉ ሲሆን፤ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ነገ በሚኖረው  ቆይታ 35 የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች እንደሚቀርቡ የሚጠበቅ መሆኑ ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም