ቀጥታ፡

ብልጽግና ፓርቲ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል እንዲለወጥ እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የያዘውን ቁርጠኝነት የሚያመላክት ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 17/2016(ኢዜአ)፦ብልጽግና ፓርቲ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል እንዲለወጥ እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎችና  እየተገኙ ያሉ ውጤቶች ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የያዘውን  ቁርጠኛ አቋም የሚያሳይ መሆኑን የፓርቲው የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ መለስ ዓለሙ ገለጹ። 

ፓርቲው አለመግባባቶች በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲፈቱ የጸና አቋም እንዳለውም ተናግረዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ መለስ ዓለሙ፤ ፓርቲው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር እንዲሰፋ በርካታ እርምጃዎች መውሰዱን ለኢዜአ ገልጸዋል።

የመንግስት ስልጣን ሽግግር በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲሆንና ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሐዊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ያከናወነው ስራ ለዴሞክራሲ ባህል መዳበር አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል።

በፓርቲው የውስጥ ዴሞክራሲን የማጎልበት ስራ፤ የዴሞክራሲ ስርዓትን መገንባትና ማጽናትን ዓላማ የያዘ ነው ብለዋል።

ፓርቲው የዴሞክራሲ ተቋማት ነጻና ገለልተኛ ሆነው እንዲሰሩና ዜጎች በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድም ውጤታማ ስራዎችን መከናወናቸውን አስረድተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቋማዊና ሎጅስቲካዊ አቅም እንዲጠናከር በማድረግ የዴሞክራሲ ባህል እንዲጎለብትና የፖለቲካ ምህዳር እንዲሰፋ ከፓርቲዎቹ ጋር በትብብር እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ብልጽግና ፓርቲ እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ነው ያሉት ኃላፊው።

ብልጽግና ፓርቲ ለችግሮች መፍትሄ የሚገኘው በሰላማዊ መንገድ በሚደረግ ትግል ነው ብሎ እንደሚያምን ገልጸው፤  በኃይል የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት የሚደረግ ጥረት ኢትዮጵያና ሕዝቧቿን አይመጥንም ብለዋል።

ማንኛውም ጉዳይ በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ውይይትና በሀሳብ የበላይነት ይፈታል ብሎ እንደሚያምንም አብራርተዋል።

ፓርቲው ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት የያዛቸውን አቋሞች በማጠናከር በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ እንዲጎለብት እንደሚሰራ ተናግረዋል። 

የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በአንድ ጀምበር የሚሳካ አይደለም ያሉት ኃላፊው፤ ሕብረተሰባዊና ተቋማዊ ለውጦች እንደሚያስፈልጉ አንስተዋል።

ጠንካራ የዴሞክራሲ አስተሳሰብ መገንባት፣ ለዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበት የሚያግዙ የሕግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀትና ሌሎች የፖለቲካ ባህሉን የሚያሳድጉ አስቻይ ሁኔታዎች መፍጠር ላይ  በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ሰላማዊ ትግልና የሕግ የበላይነት ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው ያሉት ኃላፊው፤ ይህም እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ እንዲሳካ ብልጽግና ፓርቲ የማይናወጥ አቋም እንዳለውና በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም