ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለባለድርሻ አካላት ገለፃ አደረገ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 17/2016(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከተማ በሚካሄደው የምክክር ምዕራፍ ላይ ለሚሳተፉ ባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለፃ አደረገ፡፡

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገ/ስላሴ ኮሚሽኑ ዛሬ የተገኙትን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን አሳታፊነት እና አካታችነት እንደ ዋነኛ መርሆዎቹ አድርጎ በመለየት እስካሁን በነበሩት ስራዎቹ በአጋርነት አብሮ ሲሰራ መቆየቱን ገልፀዋል፡፡

የዛሬው መድረክም ከግንቦት 21 እስከ 27/2016 በአዲስ አበባ ከተማ ለሚካሄደው የምክክር ምዕራፍ ባለድርሻ አካላት ከኮሚሽኑ ጋር ተባብረው የሚሰሩበትን የአሰራር ስርዓቶች እና የምክክር ሂደቶችን በተመለከተ ግንዛቤ ለማስጨበጥ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡

በዛሬው ገለፃ ከመንግስት ሰራተኞች፣ ከቀድሞ ሰራዊት አባላት፣ ከዳኞች፣ ከአካል ጉዳተኞች፣ ከመንግስት ስራ አስፈፃሚ አካላት፣ ከመምህራን ማህበር፣ ከንግድ ዘርፍ ማህበራት፣ ከአሰሪዎች ማህበራት እንዲሁም ከወጣቶች እና ሌሎች አደረጃጀቶች የመጡ ተባባሪ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

በመድረኩ የኮሚሽኑ የእስካሁን የስራ እንቅስቃሴ እና የወደፊት የትኩረት አቅጣጫዎችን የተመለከተ ገለፃ ለተሳታፊዎች ቀርቦ ውይይት መደረጉን ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም