የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሰኔ 10 ጀምሮ ወደ ነቀምቴ በረራ ይጀምራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሰኔ 10 ጀምሮ ወደ ነቀምቴ በረራ ይጀምራል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 17/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ከሰኔ 10/2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ኦሮሚያ ክልል ነቀምቴ ከተማ በረራ እንደሚጀምር ገለጸ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቀደም ሲል በነቀምቴ ከተማ ከአራቱም የወለጋ ዞኖች ከተውጣጡ ነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ኅብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የተለያዩ ልማት ጥያቄዎች ለመፍታት መንግሥት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ መግለጻቸው ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ ወደ ነቀምቴ በረራ ለማስጀመር የኢትዮጵያ አየር መንገድ አበክሮ ሲሰራ የቆየ ሲሆን ከመጪው ሰኔ 10/2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ነቀምቴ በረራውን እንደሚጀምር ገልጿል።
አየር መንገዱ የንግድ ዘርፍ ዋና ኃላፊ ለማ ያዴቻ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ አየር መንገዱ እያደገ የመጣውን የአገር ውስጥ የደንበኞች ፍላጎት ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ነው።
በዚህም ከመጪው ሰኔ 10/2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ነቀምቴ በረራ እንደሚጀምር ገልጸው በረራው በሣምንት አራት ጊዜ እንደሚካሄድ ነው ያብራሩት።
አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹን ከማስፋት ባሻገር የአገር ውስጥ መዳረሻዎችን ለማስፋት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም 2035 የአገር ውስጥ መዳረሻዎቹን ወደ 32 ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባሉት ከ144 አውሮፕላኖች ከ136 በላይ ዓለም አቀፍና 22 የአገር ውስጥ መዳረሻዎችን እየሸፈነ ይገኛል።