ተቋማት ለአካቶ ትግበራ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ የክትትልና ቁጥጥር ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ተቋማት ለአካቶ ትግበራ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ የክትትልና ቁጥጥር ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 17/2016(ኢዜአ)፦ ተቋማት ለአካቶ ትግበራ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ የክትትልና ቁጥጥር ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዩኤን ውመን(UN Women) ጋር በመተባበር ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን በተመለከተ ውይይት እያደረገ ነው።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቅሰሙ ማሞ በዚሁ ጊዜ፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አካታችነትን፣ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የጀመራቸው ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይ ተቋማት ለሥርዓተ ጾታ ጉዳይ እንዲሁም ለተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎች ትኩረት ሰጥተው እንዲያቅዱና እንዲያስፈጽሙ ምክር ቤቱ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የነበሩባቸውን ችግሮች በመፍታት በሁለንተናዊ መልኩ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው።
የእነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ በሁሉም ዘርፍ አካታች በሆነ መልኩ ለመተግበር መልካም ጅምሮች መኖራቸውን ጠቅሰው እስካሁን የተሰሩ ሥራዎች የሚፈለገው ደረጃ ላይ አለመድረሱን ገልጸዋል።
ይህንንም ተከትሎ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማካተትና ተጠቀሚነታቸውን በማረጋገጥ ረገድ የሚሰሯቸውን ሥራዎች በአግባቡ እየተቆጣጠረና እየተከታተለ መሆኑን አንስትዋል።
በዚህም ተቋማቱ የበጀት እጥረት፣ የቁርጠኝነት፣ የክህሎትና የተጠያቂነት ሥርዓትን በአግባቡ ያለማስፈን ክፍተቶች እንዳሉባቸው ለማወቅ ተችሏል ነው ያሉት።
በዘርፉ የአደረጃጀት፣ የመዋቅርና የሰው ኃይል ችግሮችም እንደሚስተዋልባቸው ገልጸዋል።
በመሆኑም ተቋማት አካቶ ትግበራ ሂደቱ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን መሥራት እንዳለባቸው ተናግረው በዚህ ረገድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በተለይም ተቋማት እቅድ በሚያዘጋጁበት ወቅት ለሥርዓተ ጾታ እንዲሁም ተጋላጭ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ትኩረት የሰጠ እንዲሆን በክትትልና ቁጥጥር ሥራቸው እንዲያረጋግጡ ጥሪ አቅርበዋል።