የአየር ሁኔታ ትንበያ መረጃዎችን ለልማት በማዋል ረገድ ተቋማት ልምዳቸውን ማጎልበት እንዳለባቸው ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የአየር ሁኔታ ትንበያ መረጃዎችን ለልማት በማዋል ረገድ ተቋማት ልምዳቸውን ማጎልበት እንዳለባቸው ተገለጸ
አሶሳ፤ ግንቦት 17/2016 (ኢዜአ) )፡- የአየር ሁኔታ ትንበያ መረጃዎችን በአግባቡ በመጠቀም ለልማት ለማዋል ተቋማት ልምዳቸውን ማጎልበት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።
ኢንስቲትዩቱ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የበልግ ወቅት እና የክረምት ወራት የአየር ትንበያት ላይ የሚመክር መድረክ በአሶሳ ከተማ እያካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በወቅቱ እንዳሉት ኢንስቲትዩቱ የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ የአየር ሁኔታ ትንበያ መረጃዎች በተከታታይ እያቀረበ ነው።
''የአየር ሁኔታ ትንበያ መረጃ በድንበር አይወሰንም'' ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ዓለም አቀፍ መረጃዎችንም ኢንስቲትዩቱ እንደሚያሰራጭ አመልክተዋል።
መረጃዎቹን በአግባቡ መጠቀም ምርት እና ምርታማነትን ከማሳደግ ባሻገር በህይወት እና ንብረት ላይ የሚደርስ ጉዳት መቀነስ የሚያስችል እንደሆነም አብራርተዋል።
በተለይ የትንበያ መረጃው ለግብርና ቢሮዎች፣ የውሃ ሃብት የሚያስተዳድሩ አካላትና ጤና ተቋማት ዋነኛ ግብዓት ሊሆናቸው እንደሚችል ጠቅሰው፤ መረጃው ለዕለት ተዕለት እንቅስቃሴም ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
ተቋማት ከኢንስቲትዩቱ ጋር የበለጠ በመቀራረብ እና የአየር ትንበያ መረጃዎችን በአግባቡ በመጠቀም ለልማት የማዋል ልምዳቸውን የበለጠ ማሻሻል እንዳላበቸው ገልጸዋል።
በኢንስቲትዩቱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሚትዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ሰለሞን በበኩላቸው፤ ማዕከሉ ክልላዊ የአየር ሁኔታ እና የአየር ጸባይ ትንበያ መረጃዎችን በማቅረብ የድርሻውን እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢንስቲትዩቱ ለአሶሳ ቅርንጫፍ በ30 ሚሊዮን ብር ባለሁለት ወለል ህንጻ ያስገነባ ሲሆን ይህም የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሸል የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይ በክልሉ የተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት የተውጣጡ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።