በተፋሰስ ልማትና ከባቢያዊ ምቹነት ዙሪያ የተከናወኑ ተግባራት ለዓለም አቀፍ የብዝሀ ህይወት ጥበቃ አስተዋጽኦ አበርክተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በተፋሰስ ልማትና ከባቢያዊ ምቹነት ዙሪያ የተከናወኑ ተግባራት ለዓለም አቀፍ የብዝሀ ህይወት ጥበቃ አስተዋጽኦ አበርክተዋል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 17/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ በተፋሰስ ልማትና ከባቢያዊ ምቹነት ለመፍጠር የተከናወኑ ተግባራት ለዓለም አቀፍ የብዝሀ ህይወት ስምምነት ስኬት የላቀ አበርክቶ እንዳላቸው የኢትዮጵያ ብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ስምምነቱን በአግባቡ ተግባራዊ እያደረጉ ካሉ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያን ቀዳሚ እንዳደረጋት ኢንስቲትዩቱ ገልጿል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፈለቀ ወልደየስ(ዶ/ር) ለኢዜአ አንደገለጹት የሰው ልጆች የእለት ኑሮ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከብዝሀ ሕይወት ጋር የተቆራኘ ነው።
ለሰው ልጆች መሠረታዊ ፍላጎት መሟላት፣ ለተፈጥሮና አካባቢያዊ ምቹነት የብዝሀ ሕይወት አስተዋጽዖ ከፍተኛ መሆኑንም አብራርተዋል።
የብዝሀ ህይወት ጥበቃን በተመለከተ ኢትዮጵያ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በመፈረም ለዘርፉ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን በመጥቀስ በዋናነት ከ30 ዓመት በላይ ያስቆጠረው ዓለም አቀፍ የብዝሀ ህይወት ስምምነት አንዱና ዋነኛው መሆኑንም ጠቁመዋል።
የስምምነቱ ዋነኛ ዓላማዎች የብዝሀ ህይወት ሃብትን ማስጠበቅ፣ ዘለቄታዊ አጠቃቀምንና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ መሆናቸውንም ምክትል ዳይሬክተሩ አክለዋል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለው ተግባር በአርአያነት የሚነሳና ለስምምነቱ ስኬት አሻራ የሚጥል ነው ብለዋል።
በተለይም በተፋሰስ ልማት የሚከናወኑ ተግባራት የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡና ዓለም አቀፍ ስምምነቱን የሚያሳኩ ናቸው ነው ያሉት።
በተጨማሪም ከቅርብ አመታት ወዲህ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለብዝሀ ህይወት መጠበቅ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት ይበልጥ ለማሳደግና የዘርፉን ጥቅም ለማጎልበት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል ብለዋል።
በዋናነት ሀገሪቱ የፈረመቻቸውን ዓለም አቀፍ የብዝሀ ህይወት ስምምነቶች ተግባራዊ በማድረግ በአግባቡ የመፈጸም አቅሟን ያሳየችበት እንደሆነም ተናግረዋል።