ቀጥታ፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት 2ሺህ 371 የምግብ አይነቶች የገበያ ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 17/2016(ኢዜአ)፦ በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት 2 ሺህ 371 የምግብ አይነቶች በምዝገባ የገበያ ፈቃድ እንደተሰጣቸው የኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ የምግብ ዘርፍ ምክትል ዳሬክተር አቶ ነጋሽ ስሜ ለኢዜአ እንዳሉት፤ባለስልጣኑ የምግቦችን ጥራትና ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተቀናጀና የተጠናከረ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። 

ህገ-ወጥ የምግብ ንግድ ዝውውርና ምግብን ከባዕድ ነገር መቀላቀልን ከመቆጣጠር አንጻር የቁጥጥር ስራው በተጠናከረ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል። 

ለቁጥጥር ስራው ደረጃውን የጠበቀ የምግብ ላቦራቶሪ በማደራጀት በቴክኖሎጂ በመደገፍ  እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።  

በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት መስፈርቶችን ላሟሉ 2 ሺህ 371 የምግብ አይነቶች ተመዝግበው የገበያ ፈቃድ እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸዋል።

ፍቃድ ያገኙት ድርጅቶች የአገር ውስጥ አምራች ድርጅቶች እና ከውጭ የሚያስመጡ እንደሆኑ ጠቁመዋል።

ፍቃድ ካገኙ የምግብ አይነቶች መካከል የለስላሳ መጠጦች፣ የታሸጉ ምግቦች፣ የታሸገ ውሃ፣  የለውዝ ቅቤ እና ጣፋጭ ምግቦች ለአብነት እንደሚገኙበት ገልጸዋል። 

በምግብ አይነቶች የምዝገባ ፍቃድ መስጠት ከጀመረ ከአራት ዓመታት በላይ እንደሆነና በዚህ ጊዜ ውስጥ ከ 6 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የምግብ አይነቶች ፍቃድ መስጠቱን ነው ያብራሩት።   

የምግብ ደህንነት እና ንፅህና ለንግድ ስራ በጣም አስፈላጊ በመሆኑ በዚህ ረገድ ለምግብ አማራቾች ባለፋት 9 ወራት የብቃት ማረጋገጫ መሰጠቱን ገልጸዋል።

በዚህም በዘጠኝ ወራት ውስጥ 89 የሚሆኑ የአገር ውስጥ የምግብ አምራቾች የብቃት ማረጋገጫ መውስዳቸውን ገልጸዋል።

ተቋሙ በምግብና በጤና ግብዓቶች ቁጥጥር ስራ ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን በማግኘት በአፍሪካ የልህቀት ማዕከል የመሆን ራዕዩን ለማሳካት አበክሮ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ደህንነቱ ያልተጠበቀ ምርት ወደ ገበያ እንዳይወጣ የሚደረገው ቁጥጥር በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚደረግ ገልጸው የሀገር ውስጥ አምራቾች ምርታቸውን በማስመዝገብ የብቃት ማረጋገጫ ማውጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም