ወለጋ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢው የማዕድን ልማት ስራ በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን በጥናትና ምርምር እያገዘ ነው

ነቀምቴ ፤ ግንቦት 17/2016 (ኢዜአ)፡- ወለጋ ዩኒቨርሲቲ በወለጋና አካባቢው የማዕድን ልማት ስራ በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን በጥናትና ምርምር ለማገዝ እየሰራ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀሰን የሱፍ ገለጹ።

ዩኒቨርሲቲው ''የአመራረት ቴክኖሎጂዎች፣ ማዕድን ማውጣትና ግኝት ለዘላቂ ልማት" በሚል ሀሳብ ሀገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስና አውድ ርዕይ እያካሄደ ነው።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀሰን የሱፍ፣ ዩኒቨርሲቲው የማዕድን ሀብት ልማት በእወቅትና በቴክኖሎጂ ታግዞ ጥቅም ላይ እንዲውል የጥናትና ምርምር መድረክ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።


 

በተለይም ዩኒቨርሲቲው በሚገኝበትና ወለጋና አካባቢው በርካታ የማዕድን ሀብት መኖሩ በተለያየ ጊዜ በተደረጉ ጥናቶች መረጋገጡን ተናግረዋል።

በእነዚህ አካባቢዎች የማዕድን ሀብት ልማት በባህላዊ መንገድ የሚከናወን በመሆኑ ሀብቱ በአግባቡ ለሀገር ጥቅም እየዋለ አለመሆኑን አንስተዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር በአካባቢው ያለው የማዕድን ሀብት በዘመናዊ መንገድ እንዲለማ በጥናትና ምርምር ለማገዝ የጀመረውን ስራ ያጠናክራል ብለዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም በአካባቢው ያለውን ጸጋ ተረድተው በጥናትና ምርምር ስራዎች እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።


 

በዩኒቨርሲቲው የጂኦሎጂ መምህር ደግፍ ተመስገን፣ በወለጋና አካባቢው የተለያዩ የተፈጥሮ ማዕድናት ይገኛሉ ብለዋል።

በአካባቢው ዜጎች ለአመታት በባህላዊ መንገድ እንደ ወርቅ የመሳሰሉ ማዕድናትን ሲያወጡ እንደነበረ ጠቅሰው፣ አመራረቱን ለማዘመን ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላዋ ዩኒቨርሲቲው የጂኦሎጂ መምህርት ሀና ታምሩ፣ የማዕድን ልማት ስራ ቅንጅታዊ አሰራርን የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ይህም በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ከመንግስት፣ ከባለሀብቶች እና የማዕድን ሀብት በሚገኝባቸው አካባቢው ያሉ ዜጎች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሁሉም አካባቢ ያሉ ምሁራን ኢትዮጵያ ካላት የማዕድን ሀብት በአግባቡ ተጠቃሚ እንድትሆን የበኩላቸውን ጥረት ማድረግ አለባቸው ሲሉም መክረዋል።

በዩኒቨርሲቲው የተዘጋጀው የጥናትና ምርምር ኮንፍረንስ ለሁለት ቀናት እንደሚቆይ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም