የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፋሲል ከነማ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፋሲል ከነማ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 16/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ26ኛ ሳምንት የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፋሲል ከነማ ጋር ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከቀኑ 9 ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳል።
በአሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 25 ጨዋታዎች 16 ጊዜ ሲያሸንፍ 4 ጊዜ ተሸንፏል። 5 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
በ25ቱ ጨዋታዎች 49 ጎሎችን ሲያስቆጥር 24 ግቦች ተቆጥረውበታል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት 5 ተከታታይ ጨዋታዎች 4 ጊዜ ሲያሸንፍ 1 ጊዜ አቻ ወጥቷል። በነዚህ 5 ጨዋታዎች 12 ግቦችን ሲያስቆጥር 4 ግቦችን አስተናግዷል።
ክለቡ በ53 ነጥብ በመሰብሰብ የሊጉ መሪ ነው።
ተጋጣሚው ፋሲል ከነማ በሊጉ ባከናወናቸው 25 ጨዋታዎች በ10ሩ ሲያሸንፍ 5 ጊዜ ሽንፈት አጋጥሞታል። 5 ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። በጨዋታዎቹ 33 ግቦችን ሲያስቆጥር 23 ጎሎችን አስተናግዷል።
ቡድኑ ካለፉት 5 የሊግ ጨዋታዎች 2 ጊዜ ሲያሸንፍ 3 ጊዜ አቻ ወጥቷል። በ5ቱ ጨዋታዎች 5 ግቦችን ከመረብ ሲያሳርፍ 3 ግቦች ተቆጥሮበታል። ፋሲል ከነማ በ40 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ከተከታዩ መቻል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት ከፍ ያደርጋል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 4 ለ 2 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
በሌላኛው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 26ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ሲዳማ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሲዳማ ቡና በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች 2 ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ 2 ጊዜ ተሸንፏል። 1 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል። በ5ቱ ጨዋታዎች 6 ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ 6 ግቦችን አስተናግዷል።
በዘላለም ሽፈራው የሚሰለጥነው ሲዳማ ቡና በ31 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የአምናው የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካለፉት 5 የሊግ ጨዋታዎች 3 ጊዜ ሲሸነፍ 2 ጊዜ አቻ ወጥቷል። በነዚህ 5 ጨዋታዎች 3 ጎሎችን ሲያስቆጥር 6 ግቦችን አስተናግዷል።
በጊዜያዊ አሰልጣኝ ደረጀ ተስፋዬ የሚመራው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ40 ነጥብ ተመሳሳይ የነጥብ ብዛት ያለውን ፋሲል ከነማን በግብ ክፍያ በልጦ 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር በሊጉ ባደረጉት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ 1 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል።
በተያያዘም ትናንት በተደረጉ የ26ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መቻል እና ሻሸመኔ ከተማ ሁለት አቻ ሲለያዩ ባህር ዳር ከተማና ወላይታ ድቻ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።