የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከአራት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የኢኖቬሽን ተግባራትን በትብብር ማከናወን የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 17/2016(ኢዜአ)፦ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከጅማ፣ ድሬድዋ፣ ሐዋሳ እና ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የኢኖቬሽን ተግባራትን በትብብር ማከናወን የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።

በዝግጅቱ ላይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ስምምነቱ በኢኖቪዝ-ኬ ኢንኩቤሽን ማዕከል እና በዩኒቨርሲቲዎች ያሉ አቅሞችን አቀናጅቶ በመጠቀም በዘርፉ ውጤት ማምጣት አላማ ያደረገ ነው ብለዋል።


 

የሚከናወኑ የምርምር፣ የኢኖቬሽን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ስታርታፖችን የመደገፍ ብሎም ምቹ ስነ-ምህዳር ከመፍጠር አንጻር ያሉ ስራዎችን በጋራ በመስራት ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ዘርፉ የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ለማበርከት ያግዛል ብለዋል።

በፊሪማ ስነ-ስርአቱ ላይ ድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ኡባህ አደም(ዶ/ር) ስምምነቱ ዩንቨርሲቲዎች የሰው ሃይል ልማት ስራቸውን በተቀናጀ መንገድ ለመስራት አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት።

ዩኒቨርሲቲዎች ያላቸውን አቅም በሀገር ኢኮኖሚ ልማት ለማዋል በዚህ መልኩ ተባብሮ መስራት ፈጥኖ ውጤታማ ስራዎችን ለመስራት እንደሚያግዝ የተናገሩት ደግሞ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጀማል አባ ፊጣ(ዶ/ር) ናቸው።

የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ታፈሰ ማትዮስ(ዶ/ር) ዩንቨርሲቲው በፈጠራ በምርምር እና በቴክኖሎጂ ስራዎችን ለመስራት ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት ጠቅሰው ይህን መሰል ቅንጅት መፈጠሩ ያሉ አቅሞች እንዳይባክኑ ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል።

የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት አዝመራው አየሁ(ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲው ከሚኒስቴሩ ጋር በርካታ ውጤታማ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

ይህ ስምምነትም የነበሩ ሰራዎችን ከማጠናከር ባለፈ ዩኒቨርሲቲው አቅሙን እንዲጠቀም ያግዘዋል ብለዋል።

ከስትራይድ ኢትዮጵያ 2016 ኤክስፖ (STRIDE Ethiopia 2024 Expo) ጎን ለጎን በዘርፉ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ከምሁራን፣ ከአጋር የልማት ድርጅቶች፣ ከፈጠራ ባለሞያዎችና የግሉ ዘርፍ አንቀሳቃሾች ጋር ዘርፉን ለማጠናከር የሚረዱ ግብአቶችን ለማሰባሰብ ያለሙ ውይይቶች እየተካሄዱ እንደሚገኙ ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም