ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ከደቡብ ሱዳን ከፍተኛ የፖሊስ ልዑካን ቡድን ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ከደቡብ ሱዳን ከፍተኛ የፖሊስ ልዑካን ቡድን ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17 / 2016 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ፖሊስ አገልግሎት ኃላፊ ኢንስፔክተር ጀነራል አቲም ማሮል የተመራ ከፍተኛ የፖሊስ ልዑካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሁለቱ የፖሊስ ተቋማት ከዚህ ቀደም በተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት (MOU) መሠረት በርካታ ድጋፎችን ማድረጉንና አሁን ላይም በሪፎርሙ የተፈጠሩ ስኬቶችንና ልምዶችን ለደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ፖሊስ አገልግሎት እንደሚያጋራ ኮሚሽነር ጀነራል መግለፃቸውን የፌደራል ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ሁለቱ የፖሊስ ተቋማት የተፈራረሙትን የመግባቢያ ስምምነት (MOU) አፈጻጸም ላይ ተወያይተው በተለይ በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢ የሚስተዋለውን ሽብርተኝነት እና ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን በጋራ ለመከላከልና በትብብር አብሮ ለመስራት መስማማታቸውም ተገልጿል፡፡
ይህንን የሚያስፈጸም ቴክኒካል ቡድን በማቋቋም የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ የፖሊስ አመራሮች በቅርቡ በጋምቤላ ተገናኝተው እንደሚወያዩ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውንም ነው መረጃው ያመለከተው።
ደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ፖሊስ አገልግሎት ኃላፊ ኢንስፔክተር ጀነራል አቲም ማሮል በበኩላቸው የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ለደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ፖሊስ አገልግሎት የተለያዩ የትምህርት ዕድሎችን በመስጠት ወጣት የፖሊስ ኦፊሰሮችን ተቀብሎ እያስተማረ እንደሚገኝና ለወደፊትም ትብብሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በውይይታቸው ማንሳታቸውን ገልፀዋል።
የልዑካን ቡድኑ ግንቦት 15 ቀን 2016 ዓ.ም ተመርቆ በይፋ ሥራ የጀመረውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የዜጎች ተሳትፎ መረጃ መተግበሪያን (EFPApp) በጎበኘበት ወቅት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን እየተጠቀመ እንደሚገኝ ኢንስፔክተር ጀነራል አቲም ማሮል ተገንዝብናልም ብለዋል።
በተጨማሪም ልዑካን ቡድኑ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያን በጉበኘበት ወቅት ጠቅላይ መምሪያው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፉ የተጠርጣሪ ቃል መቀበያ ክፍሎችን አደራጅቶ ሪፎርሙን ተግባራዊ በማድረግ ሰብአዊ መብትን ያከበረ ዓለም አቀፍ ስታንደርድን የተከተለ የተጠርጣሪ አያያዝ መኖሩን ኢንስፔክተር ጀነራሉ መናገራቸውን ከፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡