ቀጥታ፡

የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያላቸው የኢንቨስትመንት ድርሻ ከ50 በመቶ በላይ ተሻግሯል - የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን 

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 16/2016(ኢዜአ)፦ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ያላቸው የኢንቨስትመንት ድርሻ ከ50 በመቶ በላይ መድረሱን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንና ናሽናል ኢንቨስትመንት ግሩፕ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ የኤሮስፔስ አካላትና መለዋወጫዎችን ማምረት የሚያስችል ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰ ስምምነቱ ኢትዮጵያ በኤሮስፔስ ቴክኖሎጂና ኢንዱስትሪ ያላትን ተሳትፎ የሚያሰፋና ዘርፉን ወደ ወሳኝ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግር ገልጸዋል።

በስምምነቱ መሰረት ናሽናል ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከ7 ወራት በፊት ለኤሮስፔስ ዘርፍ ስራ ብቻ አገልግሎት እንዲውል በተወሰነው ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተለያዩ የአውሮፕላን ክፍሎችን እንደሚያመርት አመልክተዋል።

ድርጅቱ በሊዝ በወሰደው 14 ሄክታር መሬት ላይ የሚያከናውነው የኢንቨስትመንት ስራ ከ110 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እንደሚደረግበትና ከ1 ሺህ በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የስራ እድል እንደሚያገኙ ተናግረዋል።

ኢንቨስትመንቱ ኢትዮጵያ ለአውሮፕላን አካላት የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ በማስቀረትና መለዋወጫዎችን ወደ ውጭ ለመላክ እንደሚስችል አስረድተዋል።

በተጨማሪም ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ አቅራቢያ በሚገኘው የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ተማሪዎች በኤሮስፔስና በአውሮፕላን ስሪትና በረራ ዘርፍ (ኤሮናውቲክስ) የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያደርጉበት የምርምር ማዕከል እንደሚገነባም ጠቅሰዋል።

ስምምነቱ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያላቸውን ተሳትፎ የማሳደግ አካል መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግስት በዚህ ላይ የአሰራር ማዕቀፎችን ዘርግቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


 

በዚሁ መሰረት ከሁለት ዓመት በፊት አገር በቀል ባለሀብቶች በፓርኮቹ ያላቸው ድርሻ ከ10 በመቶ በታች እንደነበር አስታወሰው፤ በተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች የባለሀብቶቹ ተሳትፎ ከ50 በመቶ በላይ መድረሱን ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው የጠቆሙት።

በተጨማሪም መንግስት በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ላይ ብቻ ተወስኖ የነበረውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት በሌሎች ዘርፎች እንዲሰፋ ለማድረግ ያከናወናቸው ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

በዚህም በአሁኑ ወቅት አገር በቀልና ዓለም አቀፍ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በፋርማሲዩቲካል ፣በተቀናጀ ግብርና፣ በማሽነሪ፣ በአውቶሞቢልና ሌሎች ዘርፎች ተሰማርተው እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የናሽናል ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ካፒቴን አበራ ለሚ ስምምነቱ በኢትዮጵያ የኤሮስፔስ ኢንዱስትሪን ለማሳደግ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው አመልክተዋል።


 

ድርጅቱ የኢንቨስትመንት ስራውን በተያዘለት ጊዜ አጠናቆ ወደ ስራ ለማስገባት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በስምምነቱ መሰረት የናሽናል ኢንቨስትመንት ግሩፕ የኤሮስፔስ (የአቪዬሽንና የሕዋ ዘርፍ ቴክኖሎጂና ኢንዱስትሪ) መገጣጠሚያ እቃዎችን አምርቶ ወደ ውጪ እንደሚልክ ተገልጿል።

የግንባታ ስራው በ18 ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል።

ናሽናል ኢንቨስትመንት ግሩፕ በቂሊንጦ የኢንዱስትሪ ፓርክ መዋዕለ ንዋይን እያፈሰሱ ከሚገኙ አገር በቀል ተቋማት አንዱ ሲሆን ተቋሙ የአቪዬሽን ትምህርት ቤትን ጨምሮ የተለያዩ ኩባንያዎችን በስሩ አቅፎ የያዘ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአውሮፕላን አካላትን በማምረት ቦይንግን ጨምሮ ለሌሎች አውሮፕላን አምራች ድርጅቶች መላክ የሚያስችለውን ስምምነት ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር በነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም መፈራረሙ የሚታወስ ነው።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም