ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባህር፣ ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ እያከናወነው ያለው ሪፎርም ደንበኞች ቀልጣፋና የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ እያስቻለ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 16/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባህር፣ ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎቱን ለማዘመን እያከናወነው ያለው ሪፎርም ለደንበኞቹ ቀልጣፋና የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ እያስቻለ መሆኑ ተገለፀ። 

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያሉ ችግሮችን በመለየት በጋራ ለመስራት የሚያስችል የደንበኞችና የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ አካሂዷል።

በዚህ ወቅት የተቋሙ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ምህረተአብ ተክሉ እንዳሉት   በወደብ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ወደአገር ውስጥ ተቋሙ   በማስገባት ለአገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ ሚና እየተወጣ  ነው ብለዋል።

ተቋሙ የሚሰጠውን አገልግሎት ዲጂታላይዝ ለማድረግ ስራ መጀመሩንና ጥራትና ደረጃን ለመጠበቅ የሚያግዙ ዘመናዊ አሰራሮችን በመዘርጋት እየሰራ እንደሆነም ተናግረዋል።

ለደንበኞች ግንዛቤ በመፍጠርና አሰራርን በማዘመን የሚወጣውን ወጪ መቀነስ ችለናልም ነው ያሉት።

ከዚህ ቀደም የኮንቴነር አማካይ ቆይታ እስከ 100 ቀን ይደርስ እንደነበር አንስተው፤ አሁን ግን በተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች ቆይታውን በመቀነስ በውጭ ምንዛሬ የሚከፈለውን ወጪ በመቀነስ በኩል ከፍተኛ ውጤት የተገኘበት ነው ብለዋል።

  ተቋሙ አገልግሎቱን ቀልጣፋ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላትና ደንበኞች ጋር ተናቦ ለመስራት መድረኮችን በማዘጋጀት በየጊዜው ውይይት እንደሚያካሂድም ጠቁመዋል። 


 

መሰል የውይይት መድረኮች አገልግሎት አሰጣጡን ዘመናዊ፣ ተደራሽ፣ ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ ለማድረግ ሚና ያለው እንደሆነም አስረድተዋል።

ለተጠቃሚዎችም ወጪና ጊዜን ለመቆጠብና ዘመናዊ አገልግሎት አሰጣጥን በመተግበር የአገር ሀበትን  ከብክነት ለመታደግ የሚያግዝ ነውም ብለዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ አካላትም ተቋሙ መሻሻሎች እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።

በመድረኩ የተሻለ አፈፃፀም ለነበራቸው ተቋማት የእውቅናና ሽልማት መርሃግብርም ተካሂዷል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም