ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን የጀመረችው ጉዞ ውጤታማ እንዲሆን ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን-የልማት አጋሮች

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 16/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን የጀመረችው ጉዞ ውጤታማ እንዲሆን የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የልማት አጋሮች ገለጹ።

የስትራይድ ኢትዮጵያ 2024 ኤክስፖ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ግንቦት 10 ቀን 2016 ዓ.ም በይፋ መከፈቱ ይታወቃል። 

  በሳይንስ ሙዚየም እየተካሄደ ካለው ኤክስፖ ጎን ለጎን "የኢትዮጵያ ሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ እና ዘላቂ የልማት ግቦችን" በተመለከተ ከልማት አጋሮች ጋር የፓናል ውይይት ተደርጓል።

በውይይቱ የተገኙት በኢትዮጵያ የተመድ የልማት ፕሮግራም የአካታች ኢኮኖሚ ልማት ቡድን መሪ አቶ ግዛቸው አስናቀ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም በኢትዮጵያ የልማት ስራዎች እየተሳተፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዋናነት ኢትዮጵያ ለጀመረችው የዲጂታላይዜሽን ጎዞ መሳካት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህንን የትብብር ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ባለሙያ ማክስም ሄንዲሪክስ በበኩላቸው የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ጎዞ ውጤታማ እንዲሆን እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ወደ ተግባር የሚገቡ እቅዶች እንዳሉ የጠቀሱት ባለሙያው፥ በአውሮፓ በዲጂታል መሰረተ ልማት ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህም የቴክኖሎጂ፣ የእውቀትና የክህሎት ሽግግርን ለማሳካት ያግዛል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ የኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ(ኮይካ) ምክትል ኃላፊ ሹንዮንግ ሊ ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በአቅም ግንባታ ዘርፍ በትብብር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ለስታርአፖች መጎልበትና ለመሰረተ ልማት መሟላት ኮይካ ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ መንግስት ፈጠራን የሚያጎለብት እና  የቴክኖሎጂ ስነ-ምህዳር እድገትን የሚደግፉ ፖሊሲዎችና ህግጋትን እየተገበረ ነው።


 

ይህም የሀገር ውስጥ ተሰጥኦዎችን በማጎልበት በቴክኖሎጂ ፈጠራ የሚመራ ዘላቂ  ኢኮኖሚ ለመገንባት ያስችላል ብለዋል።

በዚህ ሂደት ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ከልማት አጋሮች ጋር በትብብር እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም