በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ የግሉ ዘርፍ የመሪነት ሚናውን እንዲወጣ የሚያስችል ውሳኔ ተላልፏል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 16/2016(ኢዜአ)፦ በዲጅታል መር የኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ የግሉን ዘርፍ  ተሳትፎ የሚያሳድጉ ውሳኔዎች ብሔራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት መተላለፋቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት በሀገር አቀፍ ደረጃ የወጡ የዲጂታል እና ቴክኖሎጂ ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎችን ተፈፃሚነት በየጊዜው በመከታተልና በመገምገም የመፍትሔ አቅጣጫዎችን እንዲያስቀምጥ ብሔራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል።

ምክር ቤቱም ዛሬ ባካሄደው ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ሚያዚያ 4/2016 ዓ.ም ባካሄደው የመጀመሪያ መደበኛ ስብሰባው ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች አፈጻጸም በመገምገም ውሳኔዎችንና አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ተመስገን ጥሩነህ፥ ውሳኔዎቹን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ምክር ቤቱ በመጀመሪያ ስብሰባው በዲጂታል ስርዓተ ምህዳር ያሉ ህጎች፣ ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ተጠንተው እንዲቀርቡ ውሳኔ አሳልፎ እንደነበር አውስተዋል።

በዛሬው ስብሰባ በሀገሪቱ ዲጂታል ዘርፍን የተመለከቱ በርካታ ህጎች፣ መመሪያዎችና ስትራቴጂዎች ያሉ መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል።

ሆኖም እነዚህ ህጎች፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ያላቸው ተግባራዊነት እንዲሁም ለግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ክፍት ናቸው ወይ የሚለው በዝርዝር በባለሙያዎች ተጠንቶ እንዲቀርብ ውሳኔ መተላለፉን ተናግረዋል።

በተለይም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚና በዲጂታል ስርዓቱ ውስጥ የግሉ ዘርፍ የመሪነት ሚና እንዲጫወት ከማድረግ አኳያ ነባር ህጎች ምን ያህል ክፍት ናቸው የሚለው እንዲታይና አዳዲስ ህጎች እንዲዘጋጁም አቅጣጫ መቀመጡን  ነው ያነሱት።

ሌላኛው ምክር ቤቱ ያሳለፈው ውሳኔ ከኢኮኖሚና ከዲጂታል እድገት አኳያ የግሉ ዘርፍ የመሪነት ሚናውን እንዲወጣ ለማድረግ የምክር ቤቱ አባል እንዲሆን ውሳኔ መተላለፉን ገልጸዋል።

በመሆኑም ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከግሉ ዘርፍ ማህበራት ጋር በመሆን የግሉን ዘርፍ ወክለው የምክር ቤቱ አባል የሚሆኑ አካላትን እንዲያሟላ አቅጣጫ መቀመጡን ጠቅሰዋል።

ምክር ቤቱ በቨርቹዋል እየተገናኘ መወያየት እንዳለበት በመጀመሪያ ስብሰባው ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በዛሬው ስብሰባ ለቨርቹዋል የተግባቦት ስራዎች የሚያስፈልጉ መሣሪያዎችን በመለየት ውሳኔ ማሳለፉን ገልጸዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አክለውም የምክር ቤቱ አባላት በኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ውስጥ የኢትዮጵያን የዲጂታል ጉዞ የሚያሳኩ መሰረተ ልማቶች መኖራቸውን እንደተመለከቱ ገልጸዋል።

ብሔራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤቱ ለፓርኩ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ ኢትዮጵያን በአፍሪካ የቴክኖሎጂ ማዕከል ለማድረግ እንዲሰራ ይደረጋል ብለዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ለዲጂታል ሽግግሩ ወሳኝ የሆኑ የዳታ ማዕከላትና ወጣቶች የፈጠራ ሃሳቦቻቸውን ወደ ተግባር የሚቀይሩባቸው ምቹ የልምምድ ስፍራዎችን ያካተተ መሆኑን አንስተዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ፓርኩ በኢትዮጵያ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በፈጠራና በምርምር ታላቅ ሀገር እንድትሆን ይሰራል ብለዋል።


 

የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው የኢኮኖሚ ግንባታን ለማፋጠን የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ወሰኝ ሚና እንደሚጫወት ጠቅሰው፥ ሚናው እንዲጎለብትም በህግና በፖሊሲ ደረጃ መንግስት ትኩረት ሰጥቷል ነው ያሉት።


 

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ፥ በፓርኩ የሚገኙ የዳታ ማዕከላት የመንግስትና የግል ተቋማት መረጃዎችን በማከማቸትና በመጠቀም ሀገርን ወደተሻለ ምዕራፍ ለማሻገር እንደሚያስችሉ ገልጸዋል።


 

አስተዳደሩም የመረጃና የቴክኖሎጂ ደህንነትን ለማስጠበቅ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ጠቅሰዋል።

ብሔራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤቱ ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘርፍ ያቀደቻቸውን ግቦች ለማሳካት ቅንጅታዊ አሰራርን በመዘርጋትና አስፈላጊ ስራዎችን በመለየት የፖሊሲ ምክረ ሃሳብ ያቀርባል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም