የምክክሩ ተሳታፊ የማህበረሰብ አባላትን ለመመልመል ለሚያግዙ ተባባሪ አካላት በባህርዳር ከተማ ስልጠና ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
የምክክሩ ተሳታፊ የማህበረሰብ አባላትን ለመመልመል ለሚያግዙ ተባባሪ አካላት በባህርዳር ከተማ ስልጠና ተሰጠ
ባህርዳር ፤ግንቦት 16 / 2016(ኢዜአ)፡- በአጀንዳ ማሰባሰብና ምክክር ላይ የሚሳተፉ የማህበረሰብ አባላትን ለመመልመል ለሚያግዙ ተባባሪ አካላት በባህርዳር ከተማ ስልጠና መስጠቱን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ስልጠናውን የሰጠው በአማራ ክልል ሰሜን፣ ምዕራብና ምስራቅ ጎጃም ዞኖችና አዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ለተውጣጡ ተባባሪ አካላት ነው።
ሰልጣኞቹ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከመምህራን ማህበር፣ ከሲቪክ ማህበራት፣ ከእድርና ከሌሎች አካላት የተወጣጡ መሆናቸው ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም እንዳሉት፤ ኮሚሽኑ ህዝብን በማሳተፍ ችግሮች በምክክር እንዲፈቱ ለማስቻል የማመቻቸት ተግባሩን በገለልተኝነትና በነጻነት እያከናወነ ይገኛል።
ይህም በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ በሃቅ ላይ የተመሰረተ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አመልክተው፤ የዳበረ የፖለቲካ ባህል፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ቅቡልነት ያለው አገረ መንግስት በዘላቂነት ለመገንባት አስፈላጊና ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።
እስካሁንም ለህብረተሰቡ ሰፊ ግንዛቤ በማስጨበጥና የባለድርሻ አካላትን ቅንጅት በማጠናከር ለምክክሩ የማመቻቸቱ ተግባር ማስቀጠል መቻሉን ተናግረዋል።
በዚህም አዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሞች አስተዳደሮችን ጨምሮ በ10 ክልሎች የተሳታፊዎች ልየታ በማከናወን ቀጣይ ተግባራትን በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በአማራ ክልል በነበረው ችግር ቢዘገይም አሁን ህዝቡን በሚያሳተፍና አካታች በሆነ መልኩ ተሳታፊዎችን ለመመልመል የሚያግዙ ተባባሪ አካላትን በባህዳር ከተማ ማስልጠናቸውን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።
በስልጠናው ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከመምህራን ማህበር፣ ከሲቪክ ማህበራት፣ ከእድርና ከሌሎች የተወጣጡ ተባባሪ አካላትን በማሳተፍ መካሄዱን ተናግረዋል።
ተባባሪ አካላትም በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውና ውጤታማ የሆኑ ተሳታፊዎችን ለይቶ በመላክ የተጣለባቸውን ሃላፊነትና አደራ በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው ኮሚሸነሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከስልጠና በኋላ ወደ የአካባቢያቸው ተመልሰው የሚያከናውኑት ተግባር ስኬታማ እንዲሆንም የኮሚሽኑ ክትትልና ድጋፍ እንደማይለያቸው አስታውቀዋል።