በዩኒቨርሲቲዎች የሚከናወኑ የጥናትና ምርምር ስራዎችን የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እንዲፈቱ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ

አዳማ፣ግንቦት 16/2016 (ኢዜአ)፡-በዩኒቨርሲቲዎች የሚከናወኑ የጥናትና ምርምር ስራዎች ወደ ተግባር ተቀይረው የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እንዲፈቱ በቅንጅት መስራት ይገባል ሲሉ  የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።

በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ 3ኛው ሀገር አቀፍ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የምርምር አውደ ጥናት እየተካሄደ ነው።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትርና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ አቶ መላኩ አለበል በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ እውቀትና ቴክኖሎጂ ያልታከለበት ልማት ውጤታማ አይሆንም።

በዩኒቨርሲቲዎችና በምርምር ተቋማት የሚከናወኑ የጥናትና ምርምር ስራዎችም ጥራታቸውን የጠበቁ ከመሆን ባለፈ ሀገሪቷ ለያዘችው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትና እድገት ግብዓት መሆን አለባቸው ብለዋል።

የጥናትና ምርምር ስራዎች ምርታማነት፣ ለቴክኖሎጂ፣ ለእውቀትና ክህሎት ማበልጸግ አስተዋጽኦ በሚያበርክት መልኩ ሊከናወኑ እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

በተለይም ዩኒቨርሲቲዎች ከኢንዱስትሪዎች ጋር የሚኖራቸው ትስስር ሊጠናከር እንደሚገባ ጠቅሰው ለዚህ ደግሞ በዩኒቨርሲቲዎች የሚከናወኑ የጥናትና ምርምር ስራዎች የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንዲፈቱ በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል።

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲም በዚሁ ቅኝት የጀመራቸውን ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎች የበለጠ ማጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ለሚ ጉታ(ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ሃይል ለማፍራት ከሚያደርገው ጥረት ባለፈ ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በዚህም የሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ የባዮ ቴክኖሎጂ፣ የህዋና የድሮን ቴክኖሎጂን ጨምሮ የተለያዩ የልህቀት ማዕከላት መክፈቱን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በከተማ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ጥራት ማማከር እንዲሁም በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ዙሪያ ትኩረት ያደረጉ የጥናትና ምርምር ስራዎችን እያወጣ መሆኑን አስረድተዋል።

በአውደ ጥናቱ ላይ የሚቀርቡ የጥናትና ምርምር ስራዎች የሀገሪቱን ልማትና እድገት ለማፋጠን የተሰሩ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዓለሙ ዲሳሳ(ዶ/ር) ናቸው።


 

እነርሱም የኢንዱስትሪ፣ የአካባቢ ጥበቃና የአገልግሎት ዘርፍን በቴክኖሎጂ ለማስደገፍ ያለሙ የጥናትና ምርምር ስራዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ቴክኖሎጂ በሁሉም ዘርፎች ውስጥ ያለው አስተዋጽኦ ትልቅ መሆኑን ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲውም ለቴክኖሎጂ እድገት ትኩረት ሰጥቶ የጥናትና ምርምር ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት ቀናት በሚቆየው አውደ ጥናት ላይ ጥናትና ምርምሮች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸውም ተገልጿል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም