ብሔራዊ የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት የግል ዘርፉን ተሳትፎ የሚያሳድጉ ውሳኔዎችን አሳልፏል-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 16/2016(ኢዜአ)፦ ብሔራዊ የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት የግል ዘርፉን ተሳትፎ የሚያሳድጉ ውሳኔዎችን  ማሳለፉን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አስታወቁ።

ምክር ቤቱ ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ በኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ አካሂዷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የምክርቤቱ ሰብሳቢ ተመስገን ጥሩነህ፥ውሳኔዎቹን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ምክርቤቱ በመጀመሪያ ስብሰባው በዲጅታል ስርዓተምህዳር ያሉ ህጎች፣ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ተጠንተው እንዲቀርቡ ውሳኔ አሳልፎ እንደነበር አውስተዋል።

በዛሬው ስብሰባው በሀገሪቱ ዲጅታል ዘርፍን የተመለከቱ በርካታ ህጎች፣መመሪያዎችና ስትራቴጂዎች ያሉ መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል።

ሆኖም እነዚህ ህጎች፣ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ያላቸው ተግባራዊነት እንዲሁም ለግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ክፍት ናቸው ወይ የሚለው በዝርዝር በባለሙያዎች ተጠንቶ እንዲቀርብ ውሳኔ መተላለፉን ተናግረዋል።

በተለይም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚና ዲጅታል ስርዓት ውስጥ የግሉ ዘርፍ የመሪነት ሚና እንዲጫወት ከማድረግ አኳያ ነባር ህጎች ምን ያህል ክፍት ናቸው የሚለው እንዲታይና አዳዲስ ህጎች እንዲዘጋጁም አቅጣጫ መቀመጡን  ነው ያነሱት።

ሌላኛው ምክር ቤቱ ያሳለፈው ውሳኔ ከኢኮኖሚና ከዲጅታል እድገት አኳያ የግሉ ዘርፍ የመሪነት ሚናውን እንዲወጣ ለማድረግ የምክር ቤቱ አባል እንዲሆን የተወሰነ ሲሆን፤ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከግሉ ዘርፍ ማህበራት ጋር ሆኖ ሊወከሉ የሚችሉ የግሉ ዘርፍ አባላትን እንዲያሟላ አቅጣጫ መቀመጡን ጠቅሰዋል።

ምክር ቤቱ በቨርቹዋል እየተገናኘ መወያየት እንዳለበት በመጀመሪያ ስብሰባው ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በዛሬው ስብሰባ ለቨርቹዋል የተግባቦት ስራዎች የሚያስፈልጉ መሣሪያዎችን በመለየት ውሳኔ ማሳለፉን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም