ቀጥታ፡

ከየትኛውም አቅጣጫ የሚመጡ ጥቃቶችን ለመመከት የሚያስችል የተሟላ ወታደራዊ ቁመና ተገንብቷል - ጀኔራል አበባው ታደሰ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 16/2016(ኢዜአ)፦ከየትኛውም የሀገራችን አቅጣጫ የሚመጡ ጥቃቶችን ለመመከት የሚያስችል የተሟላ ወታደራዊ ቁመና መገንባቱን የጦር ሀይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ ገለጹ።

የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል ከዕዙ የተለያዩ ክፍሎች በመመልመል በአመራር ትምህርት ቤቱ ያሰለጠናቸውን ሁለተኛ ዙር የበታች ሹም አመራሮችን አስመርቋል።


 

በምረቃው ላይም የጦር ሀይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ የሀገራችንን ዕድገት የማይፈልጉ ሀይሎች በራሳቸው ያቃታቸውን ፅንፈኞችን በማሰማራት ሀገራችንን ለመበታተን ቢሞክሩም በጀግናው ሰራዊታችንና በአስተዋዩ ህዝባችን ድጋፍ ህልማቸው እንዲመክን ተደርጓል ብለዋል።


 

ሀገራችንን ለማፅናት በተከፈለው ውድ ዋጋ የመጣውን ሰላም ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ የጠቆሙት ጄኔራል አበባው ከየትኛውም የሀገራችን አቅጣጫ የሚመጡ ጥቃቶችን ለመመከት የሚያስችል የተሟላ ወታደራዊ ቁመና ተገንብቶ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ተመራቂ የበታች ሹም አመራሮችም ያገኙትን አቅም በሚመደቡባቸው ቦታዎች በመተግበር ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።


 

በዝግጅቱ ላይ የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ፣ የክልሉ የፀጥታ ዘርፍ ሀላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ ፣የሻሸመኔና የአዋሳ ከተማ ከንቲባዎች የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ ፣ የደቡብ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሰለሞን ኢተፋን ጨምሮ ከፍተኛ የሰራዊቱ አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም