ቀጥታ፡

16ኛው የፌደራልና የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች የጋራ ጉባኤ ተካሄደ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 16/2016(ኢዜአ):- 16ኛው የፌደራልና የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች የጋራ ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሄደ።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የጋራ ጉባኤውን በከፈቱበት ወቅት የክልልና የከተማ አስተዳደር ፖሊስ ተቋማት ሰላምና ደኅንነትን በማስከበር እየተሰሩ ያሉትን ተግባራት የበለጠ አጠናክሮ በማስቀጠል የሚጠበቅብንን ኃላፊነት በቅንጅት በመወጣት የሀገራችንን ሰላም እያፀናን አንቀጥላለን ብለዋል።

ኮሚሽነር ጀነራሉ ለፖሊስ ተግባር የጋራ የቴክኖሎጂ ዕድገት እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የተፈጠሩ የቴክኖሎጂ አቅሞች በአንዳንድ ክልሎች የተጀመሩ መሆኑን በመግለፅ በቀጣይ ሁሉም ክልሎች በቁርጠኝነት ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው በአፅንኦት ተናግረዋል።

በጉባኤው አሁን ላይ በሀገሪቱ ያለው ፀጥታ በጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑንና በውስን አካባቢዎች ላይ የሚታየው የፅንፈኞችና የሽብር ኃይሎች እንቅስቃሴን ለማክሸፍ የፖሊስ ኃይሉ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር ተቀናጅቶ እና ከህዝቡ ጋር ሆኖ የሕግ ማስከበር ሥራውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በጋራ መስማማታቸው ተገልጿል።

የሪፎርም ሥራው በተለይ የሰው ኃይል፣ ስልጠና እና የቴክኖሎጂ አቅምን ለማጠናከር እየተሰሩ ያሉ ተግባራት ስኬታማ መሆናቸውንና በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ሌላው የጋራ ጉባዔው የገመገመው ጉዳይ መሆኑም እንዲሁ።

በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተልዕኮ ወስዶ የተሰማራውን የፖሊስ ኃይል አቅሙን እየገነቡ በሥነ-ምግባር በማነጽ ሰብዓዊ መብትን ባከበረ መልኩ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀራርቦ እንዲሰራ እየተደረገ ያለው ውጤታማ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በጋራ ጉባኤው ምክክር እንደተደረገበትም ተጠቁሟል።

በመጨረሻም የጋራ ጉባኤው ባለፉት ወራቶች በፀጥታ እና በሪፎርም ስራዎች ላይ የታዩ አመርቂ ውጤቶች የተቀመጠውን ራዕይ ለማሳካት አመላካች መሆኑን የገመገመ ሲሆን በቀሪ ጊዜያት ይሄው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ስምምነት ላይ መደረሱን ከፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም