ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የብሪክስ ብሔራዊ የሚኒስትሮች አስተባባሪ ኮሚቴ ሁለተኛ ስብሰባውን አካሄደ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 16/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የብሪክስ ብሔራዊ የሚኒስትሮች አስተባባሪ ኮሚቴ ሁለተኛ ስብሰባውን ዛሬ ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም አካሂዷል።

የስብሰባው ዓላማ ኢትዮጵያ በብሪክስ ስብስብ ውስጥ ያላትን ተሳትፎ መገምገም እና ቀጣይ ስራዎች ላይ አቅጣጫ ማስቀመጥ መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።


 

የኮሚቴው ሰብሳቢና የኢትዮጵያ የብሪክስ ብሔራዊ ተወካይ አቶ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ ኢትዮጵያ በብሪክስ እንቅስቃሴዎች ላይ የምታደርገው ንቁ እንቅስቃሴ ለኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥቅሞች፣ ለሀገራዊ ልማት ግቦች መሳካት እና ለባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ መጠናከር ያለውን ፋይዳ አብራርተዋል።

ኮሚቴው ኢትዮጵያ በተሳለጠ ሁኔታ ወደ ብሪክስ እንድትቀላቀል የሚያስችለው የኢትዮጵያ የብሪክስ ተሳትፎ ስትራቴጂ ላይም መወያየቱ ተገልጿል።

በብሪክስ ስብስብ የመግባቢያ ስምምነት እና የኢትዮጵያ ድጋፍ መግለጫ ላይም መወያየቱ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ የብሪክስ ስብስብ አባልነት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ትብብር፣ የቴክኖሎጂ እድገት እና የሁለትዮሽ ግንኙነትን እንደሚያጠናክርም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም