ቀጥታ፡

በመንደር የንግድ ቁጥጥር የአሰራር ስርዓት ዙርያ አዲስ መመሪያ ተግባራዊ መደረግ ጀመረ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 16/2016(ኢዜአ)፦  የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ  በመንደር የንግድ ቁጥጥር የአሰራር  ስርዓት ዙርያ አዲስ ያወጣውን መመሪያ  ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን አስታወቀ።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቁጥጥር ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ  ቅድስት ስጦታው በመመሪያው ዙርያ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል ።

ኃላፊዋ በመግለጫቸው የንግድ ስርዓቱ ፍትሃዊ ፣ዘመናዊ፣ቀልጣፋና ተደራሽ እንዲሆን መመሪያው ያግዛል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ነጋዴዎችና ሸማቾች ከንግድ ስርዓቱ የሚጠበቀውን ትክክለኛ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግና ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ  ለመግታት መመሪያው መዘጋጀቱን ገልጸዋል ። 

መመሪያው የተዘጋጀው በመዲናዋ ህግን መሰረት በማድረግ ወጥ የሆነና ተጠያቂነት ያለበት ትክክለኛ የቁጥጥርና የአሰራር  ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው ብለዋል። 

በንግድ ስራ የተሰማሩ የፀና ንግድ ሥራ ፈቃድ ስለመኖሩ ለሸማች በሚታይ ቦታ ማስቀመጥ፣ የዕቃዎች ዋጋ ዝርዝር መለጠፉ ፣ ሸማቾች ለሚገዙት ዕቃ ደረሰኝ መሰጠቱ በመንደር ቁጥጥር ትኩረት የሚደረጉባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በመንደርና በወረዳ አደረጃጀት አሰራር ሥርዓት ህጉንና ደንቡን በሚተላለፉ፣ የንግድ ስራ ፈቃድ ሳይኖረው ስራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኝ፣ የንግድ ፈቃድ ሳያድስ ወይም በተሰረዘ የንግድ ፈቃድ ስራ በሚሰራ ነጋዴ ላይ በአዋጁ መሰረት በሚደረገዉ ቁጥጥርና ክትትል  አስተዳደራዊ እርምጃዎች  በተለያዩ ደረጃዎች እንደሚወሰድ ጠቅሰዋል ፡፡

በሚወሰዱ አስተዳደራዊ እርምጃዎች ላይ ቅሬታ ሲኖር ቅሬታ የመቀበል ሥርዓት በ10 ቀናት ዉስጥ እንደሚከናወን ተናግረዋል ፡፡

በቢሮ የህግ አገልግሎት ኃላፊ መለሰ ተገኑ በበኩላቸዉ መመሪያዉ ብልሹ አሰራርን ለመከላከል፣ ነጋዴው መብቱንና ግደታውን አውቆ በተረጋጋ ሁኔታ ስራውን እንዲሰራ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡

መመሪያዉ ወቅቱን የጠበቀና ትክክለኛ መሆኑን ገልጸዉ ነጋዴዉና  አስፈጻሚ አካላት ህጉን በመገንዘብ በአግባቡ እንዲመሩበት አሳስበዋል፡፡

መመሪያው አምስት ክፍሎችን የያዘ ሲሆን ጠቅላላ ድንጋጌዎች ፣ቁጥጥር የሚደረግባቸው የመንደር የንግድ ጉዳዮችና የቁጥጥር ስርዓት፣ በመንደር የአሰራር ስርዓት የቢሮ አደረጃጀቶችና የቁጥጥር ባለሙያዎች ተግባርና ኃላፊነት፣አስተዳደራዊ  እርምጃዎች  እና ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች ይዟል ።

መመሪያው በፍትህ ሚኒስቴር ተመዝግቦ ወደ ተግባር መግባቱ በዚሁ ወቅት ተገልጿል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም