የ2016 ብሔራዊ የሳይበር ተሰጥኦ ውድድር ምዝገባ ተጀመረ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 16/2016(ኢዜአ)፦የ2016  ዓ.ም ብሔራዊ የሳይበር ተሰጥኦ ውድድር  ምዝገባ ከዛሬ ግንቦት 16 ጀምሮ እስከ ግንቦት 30 እንደሚካሄድ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አስታወቀ።

አስተዳደሩ የ2016 ብሔራዊ የሳይበር ልዩ ተሰጥኦ ውድድር ፕሮግራም ምዝገባን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሳይበር ልህቀት ማዕከል ዳይሬክተር ቢሻው በየነ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ አስተዳደሩ ባለፉት ሁለት ዓመታት ታዳጊ ወጣቶችን በመመልመል ስልጠና ሰጥቶ አስመርቋል፡፡

የ2016 ብሔራዊ የሳይበር ተሰጥኦ ውድድር በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሶስተኛ ጊዜ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

የዘንድሮው ብሔራዊ የሳይበር ልዩ ተሰጥኦ ውድድር ከዛሬ ግንቦት 16 ጀምሮ እስከ ግንቦት 30 ድረስ ምዝገባው እንደሚካሄድ አመልክተዋል፡፡

ለምዝገባው እድሜያቸው ከ11 ዓመት ጀምሮ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል አቅምና ፍላጎት ያላቸው መመዝገብ እንደሚችሉ ተናግረዋል። 

የሳይበር ሴኪዩሪቲ ዘርፍ ከፍተኛ የሰው ሀይል እጥረት ያለበት መሆኑን ገልጸው ተሰጥኦ ላይ መስራት የምርጫ ጉዳይ አለመሆኑን ገልጸዋል።

መገናኛ ብዙሀን፣ የትምህርት ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍ እንዲሁም ቁልፍ የመንግስት ተቋማት ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም