ቀጥታ፡

የአፈር ማዳበሪያ ቀድመው በማግኘታቸው ለዘር ስራ ዝግጅት አመቺ እንደሆነላቸው በአማራ ክልል  አርሶ አደሮች ገለጹ

በህር ዳር ፤ ግንቦት 16/2016(ኢዜአ)፦  በዘንድሮው የመኽር ወቅት ለሚያከናውኑት የሰብል ልማት የሚያስፈልጋቸውን ማዳበሪያ ቀድመው  ማግኘት በመቻላቸው ለዘር ስራ ዝግጅት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው  በአማራ ክልል አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አርሶ አደሮች ገለጹ።

በክልሉ ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ማሰራጨት መቻሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል።

በደቡብ ጎንደር ዞን የእስቴ ወረዳ አርሶ አደር ሞገስ ሲሳይ እንዳሉት፤ ባለፈው ዓመት ባጋጠማቸው የማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት የሰብል ልማት በተገቢው ለማካሄድ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሮባቸው ነበር።

የክልሉ መንግስት ዘንድሮ የማዳበሪያ ፈጥኖ በማቅረቡ ቀድመው ለሚዘሩት ሰብል 2 ኩንታል ተኩል ማዳበሪያ መግዛት እንዳቻሉ ገልጸዋል።

ዝናቡ በአካባቢው ቀድሞ መጣል መጀመሩን ጠቅሰው፤ በዚህም ሶስት  ሄክታር ተኩል መሬት በማረስ ከዚህ ውስጥ አንድ ሄክታር መሬት በገብስ ዘር መሸፈናቸውን ተናግረዋል። 


 

ቀሪውን መሬት በቢራ ገብስና በስንዴ ሰብል በመሸፈን ባለፈው ዓመት በግብዓት እጥረት ያጡትን ምርት ሊያካክስ የሚችል ምርት ለማግኘት እንደሚጥሩ አስረድተዋል። 

በምዕራብ ጎጃም ዞን የወንበርማ ወረዳ አርሶ አደር ቸኮል ታደለ በበኩላቸው፤ የማዳበሪያ አቅርቦት ችግር ዘንድሮ በመሰረታዊነት መቃለሉን ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት የማዳበሪያ አቅርቦት ችግር አጋጥሟቸው እንደነበር አስታውሷ፤  ለዘንድሮው የመኽር ወቅት የሚያስፈልጋቸውን ማዳበሪያ ቀድመው  በማግኘት ለልማቱ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

ለዚህም በመኽር ወቅቱ ቀድመው ለሚዘሩት የበቆሎና ስንዴ ዘር ብዜት ስድስት ኩንታል ዳፕና ዩሪያ ማዳበሪያ መግዛታቸውን አስታውቀዋል።

ዘንድሮ ህገወጥ የማዳበሪያ ነጋዴና የደላላ ጣልቃ ገብነት በመቆሙ መንግስት ባስቀመጠው ዋጋ ግብዓት በወቅቱ ገዝተው ለግብርና ልማት ስራቸው እንዲያውሉ ያዘጋጃቸው መሆኑን ገልጸዋል። 

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አጀበ ስንሻው በበኩላቸው፤ በ2016/2017 የምርት ዘመን ለማቅረብ ከታቀደው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ  4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል ወደ ክልሉ መግባቱን ተናግረዋል።

ከዚህም  3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን አስታውቀዋል።

ቀሪው ማዳበሪያም በፍጥነት ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ አግባብ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።


 

እንዲሁም 311 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለማቅረብ ታቅዶ  187 ሺህ ኩንታል ተበጥሮ የተዘጋጀ ዘር ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ እንደሚገኝም አመልክተዋል። 

በምርት ዘመኑ በተለያየ ሰብል  ለማልማት ከታቀደው 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ መሬት ውስጥ  እስካሁንም ሦስት ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ መሬት ታርሶ የዘር ስራ እየተከናወነ መሆኑን አቶ አጀበ አብራርተዋል።

በመኽር እርሻ ዝግጅቱ 1ሺህ 892 የእርሻ ትራክተሮች ቀርበው አርሶ አደሩን እያገዙ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

በመኽር ወቅቱ በክልሉ ከሚለማው  መሬት 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ጨምረው ገልጸዋል።

በአማራ ክልል 2015/2016 የምርት ዘመን ከለማው 5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት 145  ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም