የኢትዮ-ሳዑዲ አረቢያ የሁለትዮሽ ግንኙነት መጠናከር ለቀጣናዊ ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል- አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ-ሳዑዲ አረቢያ የሁለትዮሽ ግንኙነት መጠናከር ለቀጣናዊ ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል- አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 16/2016 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ እና ሳዑዲ አረቢያ የሁለትዮሽ ግንኙነት መጠናከር ለቀጣናዊ ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ገለጹ።
አምባሳደር ታዬ ከሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፈይሰል ቢን ፋርሃን አል-ሳዑድ ጋር ውይይት አድርገዋል።
በውይይታቸውም ኢትዮጵያ እና ሳዑድ አረቢያ ያላቸውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት መሠረት በማድረግ በሰላም፣ በደህንነት፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ መስኮች ያላቸውን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ወቅቱ መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ህብረት እና ኢጋድ ጋር በመተባበር በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደህንነት እንዲሰፍን እንዲሁም ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስር እንዲፈጠር እያደረገች ላለው ተግባር ሳዑዲ አረቢያ ድጋፍ እንድታደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
አያይዘውም በሳዑዲ አረቢያ በስራ ላይ ተሰማርተው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር በመሆኑ ዜጎች መብታቸው ተጠብቆ መስራት የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት አስፈላጊ እንደሆነም አንስተውላቸዋል።
በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ትምህርት ቤቶች የሁለቱን አገራት የህዝብ-ለህዝብ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር አጋዥ በመሆናቸው የሳዑዲ አረቢያን መንግስት እገዛ ጠይቀዋል።
የሳዑዲ አረቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፈይሰል ቢን ፋርሃን አል-ሳዑድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ያላትን የረጅም ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እያደረገች ያለው ስራ በአገራቸው በኩል የሚደነቅ መሆኑን ገልፀጸው፤ የግንኙነት ደረጃው ከዚህ በበለጠ እንዲጠናከር የሳዑዲ አረቢያ ፍላጎት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ እያደረገች ያለውን አዎንታዊ የሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ ስራ በቅርበት እንደሚከታተሉት ገልፀው፣ ይህንኑ ተግባር አጠናክራ እንድትቀጥልና በጋራ ለመስራትም ዝግጁ መሆናቸውን አሳውቀዋል።
የሳዑዲ አረቢያ የቢዝነስ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት መስክ ለመሰማራት ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው መሆኑና ለስኬታማነቱም መንግስታቸው ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
በአሁኑ ወቅት አገሪቷ በኮንስትራክሽን ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ እየሰራች እንደሆነ አብራርተው ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎችን ለማሰማራት በሳዑዲ አረቢያ በኩል እቅድ መኖሩን ማሳወቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።