ቀጥታ፡

ፌደራል ፖሊስን በቴክኖሎጂ በማዘመን ወቅቱን የሚመጥን ጠንካራ ተቋም ማድረግ ተችሏል - ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 15/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስን በቴክኖሎጂ በማዘመን ወቅቱን የሚመጥን ጠንካራ ተቋም ማድረግ መቻሉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ያለማውን የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ(EFPApp) አስጀምረዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፤ ፌደራል ፖሊስን በቴክኖሎጂ በማዘመን ወቅቱን የሚመጥን ጠንካራ ተቋም ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

በዛሬው እለት ይፋ የተደረገው የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያም መረጃ መርና ማህበረሰብ አቀፍ የወንጀል መከላከል ስራን የሚያቀላጥፍ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ተቋማት በትብብር ከሰሩ የተሻለ የቴክኖሎጂ አቅም መገንባት እንደሚችሉ ያሳየ መተግበሪያ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ በሁሉም ክልሎች አገልግሎቱን ለማስፋት የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የፖሊስ አሰራር በሁሉም ረገድ እየዘመነ መሆኑን የገለፁት ኮሚሽነር ጀነራሉ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲም ወቅቱን የሚመጥን ባለሙያ በማፍራት ረገድ ከፍተኛ ሚና አያበረከተ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሀገር ባለፈ ከቀጣናው ፖሊስ ተቋማት ጋር ያለውን ትስስር ይበልጥ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም