የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ እየገነባ ያለው የዲጂታል ቴክኖሎጂ አቅም ዜጎች በወንጀል መከላከል ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ እየገነባ ያለው የዲጂታል ቴክኖሎጂ አቅም ዜጎች በወንጀል መከላከል ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ግንቦት15/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ እየገነባ ያለው የዲጂታል ቴክኖሎጂ አቅም ዜጎች በወንጀል መከላከል ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የለማውን የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ(EFPApp) አስጀምረዋል።
መተግበሪያውን ዜጎች በተንቀሳቃሽ ስልካቸው በቀላሉ በማውረድ ለፖሊስ ጥቆማ መስጠት የሚችሉበት ዘመናዊ የዲጅታል ቴክኖሎጂ ነው።
የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያው መረጃን በፎቶ፣ በተንቀሳቃሽ ምስልና በዶክመንት በቀላሉ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል መሆኑም ታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ በመርሃ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ዋነኛ ዓላማ የተቀላጠፈና የህዝብ እርካታን የሚጨምሩ አገልግሎቶችን መስጠት መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያው የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ትግበራ አካል መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን ላይ በሁሉም ተቋማት 500 የሚሆኑ አግልግሎቶች በዲጂታል ስርዓት እየተሰጡ መሆኑን ጠቅሰው በሁሉም መስኮች አየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችን በዲጂታል ስርአት በመደገፍ ይበልጥ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ በተለይ ለወጣቶች የሚሆን ሳቢ የቴክኖሎጂ አውድ መገንባት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ፌዴራል ፖሊስ ያስጀመረው መተግበሪያም አሁን ካለው የከተሞች እድገት ጋር የሚጣጣም መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የዛሬውን መተግበሪያ ጨምሮ በከተሞች የካሜራ ቁጥጥር ስርዓትና የመገናኛ ቴክኖሎጂን በማዘመን ረገድ አበረታች ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ ህዝብን ያሳተፈ የመረጃ ስርአትና የወንጀል መከላከል አቅምን የሚያጎለብት መሆኑንም ገልጸዋል።
በመሆኑም የጸጥታ ተቋማት ከራስ በፊት ለሀገርና ህዝብ በሚል መርህና በዲስፕሊን የማገልገል ተልዕኳቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አስገንዝበዋል።