ቀጥታ፡

ባለፉት ስድስት አመታት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከአናሎግ ወደ ዲጂታል ስርዓት ተሸጋግሯል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 15/2016 (ኢዜአ)፦ ባለፉት ስድስት አመታት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከአናሎግ ወደ ዲጂታል ስርዓት ተሸጋግሯል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (EFP App) አስጀምሯል ብለዋል። 

ይህ ስራ ለዜጎች መሰረታዊ አገልግሎት ለመስጠት ታልሞ የሚከናወነው የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ አካል ነው ሲሉም ገልጸዋል። 

የሁሉንም ዘርፎች ምሉዕ አቅም ለማሳካት በዲጂታል ኢትዮጵያ መደገፍ አለባቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ስድስት አመታት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከአናሎግ ወደ ዲጂታል ስርዓት ተሸጋግሯል ብለዋል። 

የህዝብ ብዛት እየጨመረ ባለበት ከተማችን ንቁ የዜጎች ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ ነው ሲሉም ገልጸዋል በመልዕክታቸው። 

ዛሬ ወደ ስራ የገባው መተግበሪያ በapp ስቶር እና playstore የሚገኝ ሲሆን ዜጎች ወንጀልን ለመከላከል በፎቶግራፍ፣ በቪዲዮ፣ በድምፅ፣ በሰነድ ወይም በቀጥታ በመደወል ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ያስችላል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ሁሉም ዜጋ የአካባቢያው እና ከተማውን ደህንነት ለማስጠበቅ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም