ቀጥታ፡

በክልሉ የሚገኙ ቋንቋዎችና ባህሎችን በጥናትና ምርምር በማስደገፍ የማልማትና የማበልፀግ ተግባር በቅንጅት እየተከናወነ ነው- ቢሮው

ቦንጋ ፤ ግንቦት 15/2016(ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሚገኙ ቋንቋዎች እና ባህሎችን በጥናትና ምርምር በማስደገፍ የማበልፀግና የማልማት ተግባር በቅንጅት እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ገለፀ ።

በክልሉ በሚገኙ ቋንቋዎችና ባህሎች ላይ በተሰሩ የምርምር ስራዎች ላይ ግብዓት የማሰባሰብ አውደ ጥናት በቦንጋ ከተማ ተካሄዷል።

አውደ ጥናቱ ”የባህልና ቋንቋ ልማት ለላቀ የህዝቦች ትስስር” በሚል መሪ ሃሳብ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ እንደገለፁት፤ በክልሉ የሚገኙ ቋንቋዎችና ባህሎችን በጥናትና ምርምር በማስደገፍ የማበልፀግና የማልማት ስራ በቅንጅት እየተሰራ ነው።

በአውደ ጥናቱም በክልሉ ከሚገኙ 13 ብሔረሰቦች ውስጥ በስምንቱ ላይ የተሰሩ 21 ሳይንሳዊ የጥናትና ምርምር ስራዎች መቅረባቸውን ገልፀዋል ።

የጥናትና ምርምር የተደረገባቸው ቋንቋዎችም ካፊኖኖ፣ ናኦ፣ ጻራ፣ ዲዚ፣ መኤንን፣ ቤንች፣ ሸኮና ዳውሮ እንደሆኑም ጠቁመዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ ወንዶሙ ኩርታ በበኩላቸው፣ በክልሉ የሚገኙ ቋንቋዎችና ባህሎችን ለማሳደግ የሚከናወኑ ተግባራትን ምክር ቤቱ እንደሚደግፍ ተናግረዋል።


 

ባህሎቹ ለህዝቦች ትስስርና አብሮነት እንዲሁም ግብረ ገብና የስራ ባህልን ከማጠናከር አንጻር ያላቸው ሚና ጥልቅ ጥናትና ምርምር ሊደረግባቸው እንደሚገባም ጠቁመዋል። 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ የባህልና ፎክሎር ተመራማሪ ዶክተር ፍሬህይወት ባዩ በአውደ ጥናቱ ላይ የምርምር ስራቸውን ካቀረቡት መካከል ይጠቀሳሉ።


 

አካዳሚው በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ቋንቋዎች ላይ ጥናት በማድረግና በመተንተን የመሰነድ ስራ እየሰራ መሆኑን ገልፀው ጥናቶቹም ለፖሊሲ ግብዓትና መነሻ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

አውደ ጥናቱ ክልሉ ከመመስረቱ በፊት የተጀመሩ የሰዋሰው፣ የመዝገበ ቃላትና ባህል ላይ የተሰሩና እየተሰሩ ያሉ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ለማጠናከር በርካታ ግብዓት የተገኘበት አውደ ጥናት መሆኑን ገልፀዋል።

በአገራችን ባህሎች ዙሪያ በርካታ ጥናቶች መሰራተታቸውን ገልፀው ይሁን እንጂ ተሰንደው ከመቀመጥ ባለፈ መሬት ላይ ወርደው አገልግሎት ላይ እንዲውሉ የማድረግ ስራ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

በአውደ ጥናቱ ላይ የናይ ብሔረሰብ ታሪክ ላይ ያተኮረ መፅሐፍን ለምረቃ ያበቃው ወጣት ተመራማሪ በፍቃዱ ሀብተማሪያም በበኩሉ፣ በባህል ውስጥ ለሀገርና ለህዝብ የሚጠቅሙ በርካታ የግጭት አፈታት ሀገር በቀል የሆኑ እውቀቶች እንዳሉ አንስቷል። 


 

በአውደ ጥናቱ የተሳተፉት የናይ ብሔረሰብ ተወላጅ አቶ ለገሰ ግዛው፣ በክልሉ ያሉ ብሔረ-ብሔረሰቦች ተወራራሽ የሆነ ቋንቋና ተቀራራቢ ባህል እንዳላቸው ተናግረዋል።

በመካከላቸው ያለውን ትስስር ከማጠናከር አንፃር እየተሰሩ ያሉ የጥናትና ምርምር ስራዎች ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው ገልፀው እንዲለማና ለትውልድ እንዲተላለፍ ማድረጉ ይበረታታል ብለዋል።

በዛሬው እለት በናይ ብሔረሰብ ታሪክ ላይ ተፅእፎ የተመረቀው መፅሐፍ ከዚህ ቀደም የነበሩ የተዛቡ አስተሳሰቦችና መረጃዎችን የሚያስተካክልና ለቀጣይ ጥናትና ምርምር እንደማጣቀሻነት የሚያገለግል ብቸኛ መፅሐፍ እንደሆነም ገልፀዋል።

በአውደ ጥናቱ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ ከክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት  ቢሮ  ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም