ቀጥታ፡

ትምህርት ቤቶች ተወዳዳሪና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሥራዎች መፍለቂያ እንዲሆኑ ትኩረት ተሰጥቷል - የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር

ሀዋሳ ፤ ግንቦት 15/2016 (ኢዜአ)፡- በሀዋሳ ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተወዳዳሪና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሥራዎች መፍለቂያ እንዲሆኑ ትኩረት መሰጠቱን የከተማው አስተዳደር  አስታወቀ።  

በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ሥር የሚገኙ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራ አውደ-ርእይ ዛሬ ተከፍቷል ፡፡


 

አውደ-ርእዩን የከፈቱት የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ መኩሪያ መርሻዬ በወቅቱ እንደገለጹት በከተማዋ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተወዳዳሪና ሀገርን የሚያሻግሩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሥራዎች መፍለቂያ እንዲሆኑ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡

አውደ-ርእዩ ለሶስተኛ ጊዜ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዝንባሌ ያላቸው እንዲሁም ችግር ፈቺና የላቀ የፈጠራ ሀሳብ የታከለባቸው ሥራዎችን መስራት የሚችሉ ተማሪዎች እንዲበረታቱ የሚያደርግ መሆኑን አመልክተዋል።

ተማሪዎች ከተማዋን ወክለው በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን እንዲችሉ የሚያደርጋቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል ።

የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ዶክተር ብርሀኑ ደሳለኝ በበኩላቸው አውደ-ርእዩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዝንባሌ ያላቸው ተማሪዎች ሀሳባቸውን ተግባር ላይ በማዋል ዕውቀትና ክህሎታቸውን እንዲያጎለብቱ መደላድል የሚፈጥር መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ዝንባሌና የፈጠራ አቅም ያላቸውን ተማሪዎች በማበረታታት ትምህርት ቤቶች የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከል እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

ተማሪዎቹ ችሎታቸውን ለሌሎች እንዲያሳዩ ብሎም እነርሱን አይተው ለፈጠራ ሥራ ለሚነሳሱ ሌሎች ተማሪዎች አርአያ እንደሚሆኑም ጠቅሰዋል ፡፡


 

አውደ-ርእዩ ለሶስት ቀናት እንደሚቆይ ጠቁመው በተለያዩ መስፈርቶች ተገምግመው አሸናፊ መሆን የሚችሉ ሥራዎችን ይዘው የቀረቡ ተማሪዎች ዕውቅናና ማበረታቻ እንደሚበረከትላቸው አስታውቀዋል፡፡

"ባለፉት ሁለት ዓመታት የሳይንስ ትምህርቶች ላይ የተማሪዎች ፍላጎትና ውጤታማነት በእጅጉ ጨምሯል " ያሉት ደግሞ በመምሪያው የመምህራን ልማት ዳይሬክተር አቶ አዳነ አብርሀም ናቸው።

መምሪያው ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር በሳይንስ ትምህርቶች መምህራን የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎችን እንዲወስዱ በማድረግ ለተማሪዎች ተገቢውን ዕውቀት እንዲያስጨብጡ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የፈጠራ ሥራቸውን ይዘው ከቀረቡ ተማሪዎች መካከል የአላሙራ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ የአብቃል መርሻ በትምህርት ቤት ደረጃ ከጓደኞቹ ጋር የሻማ ማምረቻ ፣ የባዮ ጋዝ ኃይል ማመንጫና ሌሎች ሥራዎችን ይዘው መቅረባቸውን ተናግሯል፡፡

"ለሀገራችን የሚጠቅሙ ችግር ፈቺ ሥራዎችን የመስራት ራእይ አለን " ብሏል፡፡

የዩኒየን አካዳሚ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ቤተል በቀለ በበኩሏ ለህክምና ዘርፍ የሚሆን የፈጠራ ስራ ይዛ መቅረቧን ተናግራለች።

በአውደ-ርእዩ ከ40 በላይ ትምህርት ቤቶች በሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎችን ይዘው መቅረባቸውና በአጠቃላይ ከ100 በላይ ተማሪዎች እየተሳተፉ መሆኑ ተመላክቷል ፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም