ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ "የአንድ ጤና አካሄድ" የትብብር ስርዓትን ውጤታማ ለማድረግ የትምህርትና የምርምር ተቋማት ሚና ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 15/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ "የአንድ ጤና አካሄድ" የትብብር ስርዓትን ውጤታማ ለማድረግ የትምህርትና የምርምር ተቋማት ሚና ወሳኝ  መሆኑ ተገለጸ።

የጤና ስርዓቱን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግም በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ በማካተት ማህበረሰባዊ ግንዛቤን ማሳደግ እንዲሁም በምርምር ማገዝ እንደሚገባ ተጠቁሟል።

ይህ የተባለው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከአጋር አካላት ጋር የ"አንድ ጤና አካሂድ"ን ከትምህርት ስርዓቱና ከምርምር ስራዎች ጋር ለማስተሳሰር ባካሄደው አውደ ጥናት ላይ ነው።


 

በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 529/2015 አንቀፅ 5 “አንድ ጤና አካሄድ” ማለት በሰው፣ በእንስሳት እና በአካባቢ መስተጋብር መካከል የሚከሰተውን የሕብረተሰብ ጤና ስጋቶች በተሻለ ለመከላከል፣ ለመለየት እና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ሁለገብ የትብብር ሥርዓት ነው" የሚል ትርጉም ሰጥቶታል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ፕሮፌሰር አንዱዓለም ደነቀ፣ በሀገሪቱ በሰው፣ በእንስሳትና በአካባቢ መስተጋብር ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የአንድ ጤና አካሄድ በባለድርሻዎች ትብብር እየተተገበረ መሆኑን አንስተዋል።

የጤና ትብብር ስርዓቱን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ በትምህርት ሥርዓት እና በምርምር ሥራዎች ለማካተት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ተማሪዎች በሰዎች፣ በእንስሳትና በአካባቢ መካከል ያለው መስተጋብር በጤና ስርዓቱ ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖ እንዲገነዘቡና በሽታን ቀድመው እንዲከላከሉ ስራ መጀመሩን ጠቁመዋል።

ከዚህ አኳያ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ ብቁ ባለሙያ ለማፍራት የአንድ ጤና አካሄድን በትምህርት ስርዓት በማካተት ካለፈው ዓመት ጀምሮ በሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት እየሰጠ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የሕብረሰተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ቶሌራ (ዶ/ር) የአንድ ጤና አካሄድን በትምህርት ስርዓት ውስጥ ማካተት በዘርፉ ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት እንደሚያስችል ጠቁመዋል።


 

ይህም  በሰው ልጅ፣  በእንስሳት እና በአካባቢ  መስተጋብር ውስጥ የሚፈጠረውን  ውስብስብ የጤና ችግር ለመቅረፍ አጋዥ እንደሚሆን ተናግረዋል።

በፀረ-ተህዋስያን መላመድ እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚፈጠሩ የጤና ችግሮችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚያግዙ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባም አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ  የዓለም ጤና ድርጅት የተላላፊ በሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር ባለሙያ ዶክተር ፍቃዱ አዱኛ  በኢትዮጵያ የአንድ ጤና አካሄድ አተገባበር አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።


 

ይህን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ በትምህርት ቤቶች በስፋት ስለጉዳዩ ማስተማር እና የምርምር ስራዎችን ማስፋት እንደሚገባ ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም