ቀጥታ፡

በእውቀትና በክህሎት የዳበረ ሀገር ተረካቢ ዜጋ ማፍራት የሚቻለው የንባብ ባህልን ማጎልበት ሲቻል ነው

ጋምቤላ ፤ ግንቦት 15/2016 (ኢዜአ)፦  በእውቀትና በክህሎት የዳበረ ሀገር ተረካቢ ዜጋ ማፍራት የሚቻለው የንባብ ባህልን ማጎልበት ሲቻል መሆኑን የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃሀፍት አገልግሎት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃሀፍት አገልግሎት በጋምቤላ ክልል የንባብ ባህልን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ለትምህርት፣ ለባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው 4 ሺህ 348 የማጣቀሻና የፍልስፍና መፃህፍት ዛሬ ድጋፍ አድርጓል።

የአገልግሎቱ ዋና ዳሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በእውቀትና በስነ- ምግባር የታነጸ ሀገር ተረካቢ ዜጋ ማፍራት የሚቻለው የንባብ ባህል ሲጎለብት ነው ብለዋል። 

እንደ ሀገር በእውቀትና በመረጃ የተገነባ ዜጋ ለመፍጠር እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አክለዋል።


 

ለዚህ ደግሞ ቤተ መፃህፍትን በግብዓት መደገፍና የንባብ ክበባትን ማቋቋም የንባብ ባህልን ለማሳደግ ከሚረዱ ተግባራት ዋነኞቹ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዕለቱ ለጋምቤላ ክልል ትምህርት እና ባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች የተደረገው ድጋፍ በአገልግሎት መስሪያ ቤቱ እየተከናወኑ ላሉት ስራዎች ማሳያ መሆኑን በማንሳት።

በጋምቤላ ክልል የንባብ ባህልን ለማሳደግ የህዝብ ቤተ መፃህፍትን በመገንባት ረገድ መልካም ጅምሮች መኖራቸውን ጠቁመው፤ በዘርፉ ለተጀመሩት ስራዎች መቃናት የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ የተቻለውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚደረግ ዋና ዳሬክተሩ ገልጸዋል።

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ኡቦንግ ኡቻላ በመርሃ ግብሩ ላይ እንዳሉት፤ ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት በእውቀት የተገነባ፣ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ያስፈልጋል።

በእውቀት የተገነባ ተወዳዳሪና ብቁ ዜጋ ማፍራት የሚቻለው ደግሞ ቤተ መፃህፍትን በማደራጀት የንባብ ባህልን ማሳደግ ሲቻል መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በመስኩ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ ዘርፉን ለማጠናከር  ላደረገው የመፃህፍት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።


 

በክልሉ በአብዛኛው ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን የጠበቁ ቤተ መፃህፍት ባለመኖራቸው ተማሪዎች በትርፍ ጊዜያቸው የማንበብ ልምዳቸው ውስን መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኳንግ አኳይ ናቸው።

ዛሬ በአገልግሎት መስሪያ ቤቱ የተደረገላቸው የመፃህፍት ድጋፍ የንባብ ባህልን ለማሳደግ ብቻ ሳይሆን የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየተደረገ ያለውን ጥረት በመደገፍ ረገድ የጎላ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

ድጋፍ የተደረገላቸውን መፃህፍትም ለ18  የ1ኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚሰራጩም አቶ ኳንግ ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ተዋቂ የኪነ ጥበብና ደራሲያን ባለሙያዎች ማህበር አባላት የሆኑት እንደነ ካሌብ ዋለልኝ፣ ስንቅነህ እሸቱና ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦች ለተገኙ ተማሪዎች የንባብ ልምዳቸውን አካፍለዋል።

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም