የአዘዞ ጎንደር አስፓልት መንገድ ግንባታን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የአዘዞ ጎንደር አስፓልት መንገድ ግንባታን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተገለጸ
ጎንደር፣ግንቦት 15/2016 (ኢዜአ )፡-በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ሰጪነት በአዲስ ተቋራጭ የተጀመረው የአዘዞ ጎንደር የአስፓልት መንገድ ግንባታን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ስራዎች እየተካሄዱ መሆኑን የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉና የጎንደር ከተማ አመራር አባላት የአስፓልት መንገድ ስራውን ዛሬ ተመልክተዋል።
የቢሮ ሃላፊ ዶክተር ጋሻው አወቀ እንደገለጹት፤ የመንገድ ግንባታው ሳይጠናቀቅ ለዓመታት በመጓተቱ በህዝቡ ዘንድ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል።
ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት አመራር መሰረት የቀድሞውን ተቋራጭ ውል በማቋረጥ የመንገድ ግንባታው በአዲስ እንዲጀመር መደረጉን ገልፀዋል።
"አሁን ላይ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ግንባታውን ተረክቦ በፍጥነት በማስጀመር እያካሄደ ያለው ስራ ተስፋ ሰጪና የህዝቡንም የዓመታት ቅሬታ እንደሚፈታ ማረጋገጥ አስችሏል" ብለዋል።
ዳግም የተጀመረው የመንገዱ ግንባታ የሁሉንም አጋር አካላት ተሳትፎ በማጠናከርና ተቋማዊ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ለፍጻሜ እንዲበቃ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ እገዛ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
ምልከታውም በፍጥነት የተጀመረውን የአስፋልት መንገድ አሁናዊ ሁኔታ በመገምገም ተናጥላዊና የጋራ ሃላፊነቶችን መወጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
አመራሩ በመስክ ምልከታው እንዳረጋገጠው 700 ሜትር የአስፋልት ማንጠፍ ስራን ጨምሮ በመንገዱ ግራና ቀኝ የድጋፍ ግንብና የአካፋይ መንገዶች ግንባታ ስራ በጥሩ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መገንዘብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
''የአዘዞ ጎንደር የአስፋልት መንገድ ስራ ለረጅም ዓመታት በመጓተቱ የህዝቡ የቅሬታ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል'' ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የጎንደር ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ብሩክ አዳነ ናቸው፡፡
የጎንደር ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ቀሪውን ኪሎ ሜትር የመንገዱን አካል በፍጥነት ገንብቶ እንዲያጠናቅቅ ሃላፊነት እንደተሰጠው ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅት 600 ሜትር የአስፋልት ማንጠፍ ስራ መከናወኑን ገልፀዋል፡፡
በቀጣዮቹ ሁለት ወራት የአስፋልት ማንጠፍ ስራውን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ርብርብ እንየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ከሁለት ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ የአፈር የድጋፍ ግንብ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ለግንባታ ስራው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችና ማሽነሪዎች በተሟላ ሁኔታ በማቅረብ ስራውን በተያዘለት ጊዜ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
''ለዓመታት ግንባታው ተጓቶ የቆየው የአዘዞ ጎንደር የአስፋልት መንገድ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል የተሰጠው አመራር በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ደስታ ፈጥሯል'' ያሉት ደግሞ የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሃይ ናቸው።
ከተማ አስተዳደሩ የመንገድ ስራው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ግንባታውን በባለቤትነት እንዲያከናውን ሃላፊነት ከተሰጠው የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የአዘዞ ጎንደር የአስፋልት መንገድ ግንባታ 12 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን፤ ግንባታው የተጀመረውም በ2010 በጀት ዓመት መሆኑ የሚታወቅ ነው።