በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ብረት አንስተው ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት ወደ ምክክር እንዲመጡ በድጋሜ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ብረት አንስተው ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት ወደ ምክክር እንዲመጡ በድጋሜ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 15/2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ብረት አንስተው ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት ወደ ምክክር እንዲመጡ በድጋሜ ጥሪ አቀረበ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሙሀመድ ድሪር፤ ሀገራዊ ችግሮችን በውይይት በመፍታት ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር ኢትዮጵያ የምክክር ሂደት ላይ መሆኗን ገልጸዋል።
የኮሚሽኑ የስራ ሂደት አካታችና ሁሉንም አሳታፊ በማድረግ ቀጥሎ የሀገራዊ ምክክሩ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱንም ተናግረዋል።
በእስካሁኑ ሂደት ከአማራና ትግራይ ክልሎች በስተቀር በሌሎች ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በምክክሩ ለመሳተፍ ወኪሎቻቸውን መምረጣቸውንም ጠቁመዋል።
በሁለቱ ቀሪ ክልሎችም የተሳታፊዎች ልየታ ለማካሄድ የተቀናጀ ጥረትና እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የምክክር ሂደቱ አሁን ላይ የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ ለመጀመር የሚያስችል ምዕራፍ ላይ መደረሱን ጠቁመው ተዓማኒ፣ አካታችና ገለልተኛ ምክክር እንዲኖር እየተሰራ ነው ብለዋል።
ኮሚሽነሩ በማብራሪያቸው በሀገራዊ ምክክሩ የማይሳተፍ ኢትዮጵያዊ አይኖርም ሲሉም አረጋግጠዋል።
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ብረት አንስተው ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት ወደ ምክክር እንዲመጡ በድጋሜ ጥሪ እናቀርባለን ሲሉ ተናግረዋል።
አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያን ስር ከሰደዱ ችግሮቿ ለማላቀቅና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ነፍጥ አንስተው ጫካ የገቡ ሁሉ ሰላማዊ አማራጭን እንዲቀበሉ ጠይቀዋል።
ኮሚሽኑ ግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራውን በይፋ የሚጀምር መሆኑንም ገልጸዋል።
የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ ለምታካሂደው ሀገራዊ ምክክር ድጋፉን እየቸረ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሂደቱ ሁሉም ዜጎች ንቁ ተሳትፎ በማድረግ፣ የትኛውንም ዓይነት ሀሳብ በማራመድ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚደረገው ጥረት አካል እንዲሆኑ ጠይቀዋል።