ቀጥታ፡

የካፒታል ዕቃዎች የፋይናንስ ተቋማት የሊዝ ፋይናንስ የብድር አቅርቦት እያደገ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 15/2016 (ኢዜአ)፦ የካፒታል ዕቃዎች የፋይናንስ ተቋማት የሊዝ ፋይናንስ የብድር አቅርቦት እያደገ መምጣቱ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ማኅበር የባንኮች፣ የኢንዱስትሪና የገንዘብ ሚኒስቴር ኃላፊዎች በተገኙበት በይፋ ተመስርቷል።

በማኅበሩ ምሥረታ ሥነ-ሥርዓት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር፣ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር እና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንትና የማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር)፤  ማኅበሩ ከባንኮችና ከፋይናንስ ተቋማት በማስያዣ ብድር ማግኘት ለማይችሉ ተቋማት ማኅበሩ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።

የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚገጥማቸውን የሊዝ ፋይናንስ ችግር በተቀናጀ መልኩ በመፍታት ለሀገራዊ ልማት እገዛ አድርጓል ብለዋል።

አዲስ አበባን ጨምሮ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ክልሎች ለካፒታል ፋይናንስ ምቹ ሁኔታ የፈጠረና የማሽነሪ እጥረትን ለመፍታት በጥናት የተደገፈ መፍትሔ እየሰጠ ስለመሆኑም ገልፀዋል።

በቀጣይም ማኅበሩ ሀገራዊ ልማትን የሚያፋጥኑ ተግባራትን በመደገፍ የድርሻውን ይወጣል ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ጨምሮ ማኅበሩን የመሠረቱት አምስት የካፒታል ዕቃዎች የፋይናንስ ተቋማት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2021 ከ5 ቢሊየን ብር በላይ የሊዝ ፋይናንስ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

የካፒታል ዕቃዎች የፋይናንስ ተቋማት አሁን ላይ 20 ቢሊየን ብር የሊዝ ፋይናንስ ብድር ማጽደቃቸውን ገልፀዋል።


 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ሰለሞን ደስታ፤ በኢትዮጵያ አንድ የውጭና አምስት ሀገር በቀል የካፒታል ፋይናንስ አቅራቢ ድርጅቶች መኖራቸውን ገልፀዋል።

እነዚህም ተቋማት ከ55 በላይ ቅርንጫፎችን ከፍተው ለ5 ሺህ ደንበኞች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ጠቁመዋል።

የተቋማቱ ካፒታል አቅም ከ5 ቢሊየን ብር በላይ ሲሆን እስካሁን ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ብድር መስጠታቸውን አስታውሰዋል።

በመሆኑም በቀጣይ የማምረቻ መሳሪያዎች አቅርቦት በማሳለጥ የግብርና ምርቶች ከአገር ውስጥ አቅርቦት ባለፈ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ሚናቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።


 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ በኢትዮጵያ ያለውን የሰው ኃይልና የገበያ አማራጭ በአግባቡ ለመጠቀም የሊዝ ፋይናንስ የላቀ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ገልፀዋል።

የሊዝ ፋይናንስ ኢኮኖሚውን ከማነቃቃትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ከማምጣት አኳያ ጉልህ ድርሻ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

የካፒታል ዕቃዎች ፋይናንስ ተቋማት በቂ ባለመሆናቸው ተደራሽነታቸውን ለማስፋት የግል ዘርፉ ጠንካራ ተሳትፎ ያስፈልጋል ብለዋል።

የሊዝ ፋይናንስ ተቋማት ከሀገር ውስጥ አምራቾች ማሽነሪዎችን በመግዛት የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አስፋው አበበ፤ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው መዋቅራዊ ሽግግር መሳካት የካፒታል ዕቃዎች ፋይናንስን ተደራሽ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የግብርና ምርቶች እሴት ተጨምሮባቸው ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ ማሽነሪዎችንና የግብርና ግብዓቶችን ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ማኅበርን የመሠረቱት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ የአዲስ አበባ፣ የኦሮሚያ፣ የዋልያ፣ የደቡብና የካዛ ካፒታል ዕቃ ሊዝ ፋይናንስ አቅራቢ ተቋማት ናቸው።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም