ቀጥታ፡

የቅርስ ሀብቶችን በመጠበቅና በመንከባከብ የዘርፉን ገቢ በማሳደግ ለአገር ገጽታ ግንባታ እንዲውል እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 15/2016 (ኢዜአ)፦የቅርስ ሀብቶችን በመጠበቅና በመንከባከብ የዘርፉን ገቢ በማሳደግ ለአገር ገጽታ ግንባታ እንዲውል እየተሰራ  መሆኑን  የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ።

የአፍሪካ አለም አቀፍ የቅርሶች ቀን በጢያ አለም አቀፍ መካነ ቅርስ በአህጉር ደረጃ ለስምተኛ ጊዜ  በሀገራችን ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ''ትምህርት ለአፍሪካ አለም አቀፍ ቅርሶች ጥበቃ '' በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ ነው። 

ቀኑ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣንና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና የአገር ሽማግሌዎች በተገኙበት በቡታጅራ ከተማ በፓናል ውይይትና በአውድ ርዕይ  እየተከበረ ይገኛል። 


 

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ህይወት ሀይሉ በዚሁ ወቅት አባቶቻችን ያቆዩን  ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ  ቅርሶች እሴቶቻቸውን  በመጠበቅ አሁን ያለውን ትውልድ በሚጠቅምና ለቀጣይ ለማስተላለፍ በሚችል መልኩ  በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል። 


 

ኢትዮጵያ ያላት የባህልና የተፈጥሮ ቅርሶች በመጠበቅ፣በማልማትና ለአለም በማስተዋወቅ በዘርፉ የሚገኘውን የኢኮኖሚ ገቢ የማሳደግና ለአገር ገጽታ ግንባታ የማዋል ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። 

እስካሁን በአፍሪካ አገራት በአለም ቅርስነት ከተመዘገቡ 147 ቅርሶች መካከል ኢትዮጵያ 11 ቅርሶችን በማስመዝገብ  ቀዳሚ መሆኗን  አስታውቀዋል።

የቱሪዝም ፍሰትን በመጨመር የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግና ቅርሶች ዕሴቶቻቸው ተጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፉ ሁሉም ዜጋ ሃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል። 

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አማካሪ አቶ ንጉሴ አስረስ በበኩላቸው በክልሉ ያሉ  ታሪካዊና ተፈጥሮዊ ቅርሶችን በማልማትና የቱሪስት መዳረሻ በማድረግ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) የመደመር ትውልድ መጽሀፍ ሽያጭ ለጢያ አለምአቀፍ መካነ ቅርስ ልማት እንዲውል ባደረጉት ድጋፍ አካባቢውን የማልማት ስራ መጀመሩን ገልፀዋል። 

የተባበሩት መንግስታት የትምህርት ፣ የሳይንስና የባህል ተቋም(ዩኔስኮ) እንደ እ.ኤ.አ ህዳር 2015 ባካሄደው 38 ኛው ጉባዔ ግንቦት 5 ቀን የአፍሪካ  የአለም  ቅርስ  ቀን እንዲሆን መወሰኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም