ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ዓለም አቀፍ ብቁ ተቆጣጣሪ ለመሆን የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 15/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ዓለም አቀፍ ብቁ ተቆጣጣሪ ለመሆን የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ ገለጹ።

ለዚህም የዓለም ጤና ድርጅት ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር አባላቱን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ግምገማ ማድረጉን አስታውሰዋል። 

"ማቹሪቲ ሌቭል" በዓለም ጤና ድርጅት ለጤናው ዘርፍ ተቆጣጣሪ አካላት የሚሰጥ የብቃት ማረጋገጫ ሲሆን ከአንድ እስከ አራት የሚሰጡ ደረጃዎችን ያካተተ መሆኑ ይታወቃል። 

በዓለም ጤና ድርጅት መለኪያ መሰረት "ማቹሪቲ ደረጃ 3" ያለው ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ስራውን በሚገባ የሚከወንና የተቀናጀ የቁጥጥር ስርዓት ያለው መሆኑን ያመላክታል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ፤ ኢትዮጵያን በመድኃኒት ዘርፍ የማቹሪቲ ደረጃ 3 ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

የማቹሪቲ ደረጃን ለማግኘት ከሚያስፈልጉ ሂደቶች መካከል ቅድመ ግምገማ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም የዓለም ጤና ድርጅት ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር አባላቱን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ግምገማ ማድረጉን አስታውሰዋል። 

የደረጃውን አስፈላጊነት ሲያብራሩም ደረጃ ማግኘት በራሱ ብቁ ተቆጣጣሪ ተቋም በመፍጠር የሀገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2040 የአፍሪካን የክትባት ፍላጎት 60 በመቶ በአህጉሪቱ ምርት ለመሸፈን የተያዘውን ራዕይ ለማሳካት የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል። 


 

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ስዩም ወልዴ፤ ደረጃውን ለማግኘት ባለፉት ሁለት ዓመታት የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል። 

የዓለም ጤና ድርጅት ገምጋሚዎች በኢትዮጵያ የቁጥጥር ስርዓቱን በገመገሙበት ወቅት ድርጅቱ ከዘረዘራቸው 251 አመላካቾች መካከል 209ኙ ሙሉ በሙሉ 42ቱ ደግሞ በከፊል ገቢራዊ ተደርገዋል ብለዋል፡፡

በከፊል ለተተገበሩ አመላካቾች በተሰጠው ምክረ ሃሳብ መሰረት መሻሻል አለባቸው የተባሉ 75 የሚጠጉ ጉዳዮችን በጥናት በመለየትና እቅድ በማዘጋጀት ሥራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት፡፡

በመድኃኒት ዘርፍ ኢንቨስትመንት ለመሳብና ህብረተሰቡ ጥራቱ፣ ደህንነቱና ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ መድኃኒት እንዲያገኝ ይረዳል ብለዋል። 

ባለስልጣኑ በመድኃኒት ቤቶችና መደብሮች ላይ አስገዳጅ ደረጃ ለመተግበር ከማዘጋጀትም ባለፈ፣ የተለያዩ ላቦራቶሪዎች አክሪዲቴሽን እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

ማዕከሉ የላብራቶሪ፣ የምርምርና የስልጠና ማዕከላትን ያካተተ መሆኑን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ የላብራቶሪ ግንባታው እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

የምግብ፣ መድኃኒትና ህክምና መሳሪያዎች ጥራት ቁጥጥር የልህቀት ማዕከል አንደኛ ምዕራፍ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ ለመጨረስ ክትትል እየተደረገ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡

ባለስልጣኑ ከዓለም ባንክ ባገኘው 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ድጋፍ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሚያስገነባው የልህቀት ማዕከል ግንባታ 38 በመቶ መድረሱንም ጠቅሰዋል። 

የማዕከሉ ግንባታ ህዳር 2015 ዓ.ም የተጀመረና በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም