ከሚያዚያ 2016 ዓ.ም ጀምሮ በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ከ27ሺህ በላይ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ከሚያዚያ 2016 ዓ.ም ጀምሮ በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ከ27ሺህ በላይ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 15/2016 (ኢዜአ)፦ በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ከሚያዚያ 2016 ዓ.ም ጀምሮ 27ሺህ 57 የመኖሪያ ፈቃድና ሰነድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መመለስ መቻሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ፤ በሳምንቱ የተከናወኑ ዐበይት የዲፕሎማሲ ተግባራትንና ቀጣይ ስራዎችን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ሰነድ አልባ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ስራ፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለጽዱ ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲሁም የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ የተከናወኑ ተግባራትን አብራርተዋል።
በዚህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት ይፋ ለተደረገው የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ኤምባሲዎችና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
በዚህም 20 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ለማሰባሰብ ታቅዶ እስከ ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም በአጠቃላይ 36 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰብ መቻሉን አስታውቀዋል።
ከሚያዚያ 2016 ዓ.ም ጀምሮ የመኖሪያ ፈቃድና ሰነድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ ከገባ ወዲህ 27 ሺህ 57 ዜጎችን ወደ ሀገራቸው መመለስ እንደተቻለ አስታውቀዋል።
የመኖሪያ ፈቃድና ሰነድ የሌላቸውን ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ተግባር መንግስት ለዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ የሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚያሳይ እንደሆነም አስረድተዋል።
በሌላ በኩል ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ችሎታና የስራ ክህሎትን ታሳቢ በማድረግ ለ10 ባልደረቦች የባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደርነት ለ14 ደግሞ የአምባሳደርነት ሹመት መስጠታቸውን ገልጸዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ የተመራ ልዑክ በሳዑዲ አረቢያ የስራ ጉብኝት ማድረጉን፣ ከአፍሪካ ሕብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ጸጥታ ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬንና ከካናዳ አለም አቀፍ ልማት ሚኒስትር አህመድ ሁሴን ጋር በሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ መስኮች ትብብርን ማጠናከር የሚያስችል ስኬታማ ምክክር ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከሞሮኮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሁለትዮሽ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ፉዓድ ያዙሁር፣ ከዓለም የንግድ ድርጅት የአዲስ አባል ሀገራት ድርድር የስራ ዘርፍ ዳይሬክተር ሚስ ማይካ ኦሺካዋን፣ አሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሀመር፣ በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፈን አዎር ጋር ስኬታማ የዲፕሎማሲ ምክክር ማድረጋቸውን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ምርቶች አውደ ርዕይ በደቡብ ሱዳን መዲና ጁባ መካሄዱም የኢትዮ-ደቡብ ሱዳንን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት የበለጠ የሚያሳድግ መሆኑንም አስረድተዋል።
የኢትዮ-ሩሲያን የአየር አገልግሎት ስምምነት እንዲሁም የኢትዮጵያና ኢንዶኔዢያ የስራ ስምምነት በሚኒስትሮች ምክር ቤት መጽደቁንም ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በታንዛንያ መዲና ዶዶማ የኤምባሲ አዲስ ሕንፃ ግንባታ የመሠረት-ድንጋይ በማስቀመጥ በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን አስታውቀዋል።
በቀጣይም ከተለያዩ አካላት ጋር የሚደረጉ የዲፕሎማሲና መሰል ግንኙነቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።