የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እየተመናመኑና በመጥፋት ላይ ያሉ ዕፅዋትን በመንከባከብ ለብዝሀ ህይወት ጥበቃ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው-የኢትዮጵያ ብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እየተመናመኑና በመጥፋት ላይ ያሉ ዕፅዋትን በመንከባከብ ለብዝሀ ህይወት ጥበቃ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው-የኢትዮጵያ ብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩት
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 15/2016(ኢዜአ)፦ኢንስቲትዩቱ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር እየተመናመኑና በመጥፋት ላይ ያሉ ዕፅዋትን በመንከባከብ ለብዝሀ ህይወት ጥበቃ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የኢትዮጵያ ብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩት ገለጸ።
በኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢኒስቲትዩት የደን እና ግጦሽ እጽዋት ምርምር ስራ አስፈጻሚ አበራ ስዩም ለኢዜአ እንደገለጹት ፣ ኢንስቲትዩቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተጀመረ ወዲህ ለሀገር በቀል ዕፅዋት ትኩረት በመስጠት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ሀገር በቀል ዕፅዋትን መትከል የአካባቢ ሥነ -ምህዳርን ከመጠበቅ ባለፈ በመጥፋት ላይ ያሉ ዕፅዋቶች መልሰው እንዲያገግሙ ሰፊ እገዛ እንደሚያደርግ አብራርተዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ፤የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለብዝሃ-ህይወት ጥበቃ ትልቅ እድል መሆኑን ገልጸው፤ ይህን ለማጠናከር ተቋሙ እየተመናመኑና በመጥፋት ላይ ያሉ ዕጽዋትን በመንከባከብ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ ሀገር በቀል የሆኑ ችግኞችን ኮሶ ፣ብርብራ ፣የሀበሻ ጥድ፣ ቀርቀሃንና መሰል የደን ተክሎችን ጨምሮ ለምግብነት የሚያገለግሉ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ነው የገለጹት፡፡
የተዘጋጁት ችግኞች በሙሉ ሀገር በቀል መሆናቸውን ገልጸው ፤በዘንድሮ በአረንጓዴ አሻራ ለየት የሚያደርገው ከጥላ ዛፍ በተጨማሪ ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ፓፓያና አቮካዶን ጨምሮ ሌሎች ፍራፍሬዎችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል ፡፡
ሀገር በቀል ችግኞችን መትከል የአፈር ለምነትን በመጨመር የብዝሃ ህይወትን መመናመን ለማስቀረት ትልቅ እገዛ አለው ብለዋል፡፡
ኢኒስቲትዩቱ አሁን ላይ በተለይም ለመጥፋት የተቃረቡ ዕጽዋቶችን በሀገር በቀል ለመተካት ችግኞችን በስፋት የማዘጋጀት ስራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡