የኢትዮጵያ የካፒታል ዕቃዎች የፋይናንስ ማህበር ተመሰረተ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የካፒታል ዕቃዎች የፋይናንስ ማህበር ተመሰረተ
አዲስ አበባ፤ግንቦት 15/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የካፒታል ዕቃዎች የፋይናንስ ማህበር በይፋ ተመሰረተ።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር፣ የብሄራዊ ባንክ ምክትል ገዥ፣ የገንዘብ ሚኒስቴርና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ሃላፊዎች በምስረታው ላይ ተገኝተዋል።
የማህበሩ መመስረት በኢትዮጵያ ኢንደስትሪያላይዜሽንና የግብርና መካናይዜሽንን በመደገፍ በዘርፉ የተያዙ አገራዊ ዕቅዶች እንዲሳኩ የድርሻውን ይወጣል ተብሏል።
የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚገጥማቸውን የሊዝ ፋይናንስ ችግር በተቀናጀ መልኩ ለመፍታትም እንዲሁ።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንትና የማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ ዮሃንስ አያሌው (ዶ/ር)፤ ማህበሩ ከባንኮችና ከፋይናንስ ተቋማት በማስያዣ ብድር ማግኘት ለማይችሉ ተቋማት ማህበሩ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።
አዲስ አበባን ጨምሮ በክልሎች ለካፒታል ፋይናንስ ምቹ ሁኔታ የፈጠረና የማሽነሪ እጥረትን ለመፍታት በጥናት የተደገፈ መፍትሄ እየሰጠ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
በቀጣይም ማህበሩ ሀገራዊ ልማትን የሚያፋጥኑ ተግባራትን በመደገፍ የድርሻውን ይወጣል ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ሰለሞን ደስታ፤ በኢትዮጵያ አንድ የውጭና አምስት ሀገር በቀል የካፒታል ፋይናንስ አቅራቢ ድርጅቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።
እነዚህም ተቋማት ከ55 በላይ ቅርንጫፎችን ከፍተው ለ5 ሺህ ደንበኞች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ጠቁመዋል።
የተቋማቱ ካፒታል አቅም ከ5 ቢሊየን ብር በላይ ሲሆን እስካሁን ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር መስጠታቸውን አስታውሰዋል።
በመሆኑም በቀጣይ የማምረቻ መሳሪያዎች አቅርቦት በማሳለጥ የግብርና ምርቶች ከአገር ውስጥ አቅርቦት ባለፈ አለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ሚናቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስተሩ መላኩ አለበል፤ በኢትዮጵያ ያለውን የሰው ሃይልና የገበያ አማራጭ በአግባቡ ለመጠቀም የሊዝ ፋይናንስ የላቀ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
የሊዝ ፋይናንስ ኢኮኖሚውን ከማነቃቃትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ከማምጣት አኳያ ጉልህ ድርሻ ያለው መሆኑን ጠቅሰው የካፒታል ዕቃዎች ፋይናንስ ተቋማት በቂ ባለመሆናቸው ተደራሽነታቸውን ለማስፋት የግል ዘርፉ ጠንካራ ተሳትፎ ያስፈልጋል ብለዋል።
የማህበሩ ዋና ስራ አስኪያጅ አስፋው አበበ፤ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው መዋቅራዊ ሽግግር መሳካት የካፒታል ዕቃዎች ፋይናንስን ተደራሽ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የግብርና ምርቶች እሴት ተጨምሮባቸው ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ ማሽነሪዎችንና የግብርና ግብዓቶችን ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ተመላክቷል።