ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ26ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ መካሄድ ይጀምራሉ 

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 15/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ26ኛ ሳምንት መርሐ ግብር የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። 

ወልቂጤ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

በአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት የሚመራው ወልቂጤ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ያደረጋቸውን ያለፉት 5 ጨዋታዎች ተሸንፏል።  በነዚህ 5 ጨዋታዎች 3 ግቦችን ሲያስቆጥር 11 ጎሎችን አስተናግዷል።

ወልቂጤ ከተማ በ16 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው ያለፉት 5 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው 1 ጊዜ ብቻ ነው። 2 ጊዜ ሲሸነፍ በተመሳሳይ 2 ጊዜ አቻ ወጥቷል።

ድሬዳዋ በ5ቱ ጨዋታዎች 3 ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 8 ግቦችን አስተናግዷል። 

በኮማንደር ሽመልስ አበበ የሚሰለጥነው ድሬዳዋ ከተማ በ34 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በሌላኛው የ26ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ኢትዮጵያ መድን ከአዳማ ከተማ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው ኢትዮጵያ መድን ያለፉት 5 የሊግ ጨዋታዎች አሸንፏል። መድን በነዚህ 5 ጨዋታዎች 13 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ የተቆጠረበት 1 ጎል ብቻ ነው። 

ኢትዮጵያ መድን በ31 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ተጋጣሚው አዳማ ከተማ በበኩሉ ባለፉት 5 የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት አላስተናገደም። 3 ጊዜ ሲያሸንፍ 2 ጊዜ አቻ ወጥቷል። በነዚህ 5 ጨዋታዎች 5 ግቦችን ሲያስቆጥር 2 ጎሎችን አስተናግዷል። 

በይታገሱ እንዳለ የሚሰለጥነው አዳማ ከተማ በ41 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ሁለት አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ26ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል በሊጉ 2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው መቻል ከሻሸመኔ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት፤ ባህር ዳር ከተማ ከወላይታ ድቻ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታዎችን ያደርጋሉ።

የ26ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እስከ ግንቦት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያሉ።

የሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ25 ጨዋታ በሰበሰበው 53 ነጥብ እየመራ ነው። መቻል በ50 እና ባህር ዳር ከተማ በ44 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ሻሸመኔ ከተማ በ13 ነጥብ ሀምበሪቾ በ8 ነጥብ 15ኛ እና 16ኛ ደረጃን ይዘው ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ኤርትራዊው የሃዋሳ ከተማ አጥቂ አሊ ሱሌማን በ15 ግቦች እየመራ ይገኛል። የመቻል አጥቂ ምንይሉ ወንድሙ በ12 እና የባህር ዳር ከተማው የክንፍ መስመር ተጫዋች ቸርነት ጉግሳ በ11 ግቦች ይከተላሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም